(ኢሳት ዲሲ–ነሐሴ 2/2010) የኦጋዴን ብሔራዊ ነጻነት ግንባር/ኦብነግ/ ሁሉም ወገኖች ከግጭት ራሳቸውን እንዲያርቁና ሰላማዊ መፍትሄ ላይ እንዲያተኩሩ ጥሪ አቀረበ።
ኦብነግ በጂጂጋ ባለፉት አራት ቀናት የተፈጸመውን ግድያና የቤተክርስቲያናት ቃጠሎ አውግዟል።
ድርጊቱን የፈጸሙ ግለሰቦችም ለህግ እንዲቀርቡ ጠይቋል።
መከላከያ ሰራዊቱ በመግባቱ የሶማሌ ተወላጆች ላይ አደጋ ተደቅኗል ያለው ኦብነግ የአብዲ ዒሌ ከስልጣን መወገድ ቢዘገይም ወሳኝ ርምጃ ነው ሲል ገልጿል።
የኦጋዴን ብሄራዊ ነጻነት ግንባር ኦብነግ መንግስት መከላከያ ሰራዊቱን ወደ ሶማሌ ክልል መላኩን አውግዟል።
ምክንያቱ ደግሞ የገባው ሰራዊት የክልሉን ህዝብ ለማጥቃት አቅዶ የገባ ነው የሚል ነው።
የሶማሌ ክልል መንግስት ከአቅሜ በላይ የተፈጠረ ችግር በሚል የፌደራል መንግስቱ ጣልቃ እንዲገባ ጥሪ በማድረጉ መከላከያ ሰራዊቱ መሰማራቱ ቢገልጽም የኦጋዴን ብሄራዊ ነጻነት ግንባር ርምጃው ውጥረቱን ያባባሰ ሲል አውግዞታል።
የአንድ ወገን አባላት የሆነው ሰራዊቱ በሶማሌ ተወላጆች ላይ ጥቃት ለማድረስ የገባ ነው ይላል ኦብነግ።
በተለያዩ አካባቢዎች የሚታዩት ጥቃቶች በመከላከያ ሰራዊቱ የተፈጸሙ እንደሆኑም የኦብነግ ቃል አቀባይ አቶ ሀሰን አብዱላሂ ለኢሳት ገልጸዋል።
የክልሉ ፕሬዝዳንት የነበሩትን አብዲ ዒሌን በቀላሉ በህግ ቁጥጥር ስር ማድረግ እየተቻለ ታንክ ወደ ጂጂጋ ማስገባቱ ተገቢ አይደለም ሲሉ አቶ አብዱላሂ ተናግረዋል።
የሶማሌ ክልል ፕሬዝዳንት የነበሩት አቶ አብዲ ዒሌ ከስልጣን መወገዳቸውን ያወደሰው የኦጋዴን ብሄራዊ ነጻነት ግንባር ኦብነግ የዘገየ ርምጃ መሆኑን ግን አክሎ ገልጿል።
አብዲ ዒሌን ለዚህ ደረጃ ያበቃው መንግስት ነው፡ስለዚህ ሃላፊነቱን መውሰድ አለበት ብለዋል ቃል አቀባዩ አቶ ሀሰን አብዱላሂ። በሶማሌ ተወላጆች ላይ የሚፈጸመው ጥቃት እንዲቆምም ጥሪ አድርገዋል።
በአሁኑ ሰዓት በሰላማዊ መንገድ ችግሮች መፈታት አለባቸው፡ ወደ ግጭት የሚገቡ ሀይሎች ከድርጊታቸው እንዲታቀቡ አቶ ሀሰን መልዕክት አስተላልፈዋል።
ሁሉም ወገኖች ራሳቸውን ከግጭት በማራቅ ለሰላማዊ መፍትሔ እድል እንዲሰጡ ጠይቀዋል። ባለፉት አራት ቀናት በጂጂጋና በአንዳንድ አካባቢዎች የተፈጸመውን ጥቃት ኦብነግ ማውገዙንም ቃል አቀባዩ ገልጸዋል።
በጥቃቱ ህይወታቸውን ላጡ በሙሉ ሀዘኑን በመግለጽ ግድያውን የፈጸሙና ቤተክርስቲያናትን ያቃጠሉ ሰዎች ተጣርተው ለህግ እንዲቀርቡ ኦብነግ አሳስቧል።