(ኢሳት ዲሲ–ነሀሴ 1/2010) የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ፕሬዝዳንት የነበሩት አብዲ ኢሌ ቁልፍ የልዩ ፖሊስ አመራር አባላት መታሰራቸው ተገለጸ።
ከክልሉ ፕሬዝዳንትነታቸው ተነስተው በሌላ ሰው የተተኩት አብዲ ኢሌ የኢትዮጵያ ሶማሌ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ መሪ ሆነው ይቀጥላሉ ተብሎ ነበር።
በኋላ ላይ ግን አብዲ ኢሌ በመከላከያ ሠራዊት አባላት በቁጥጥር ሥር ከዋሉ በኋላ ጅጅጋ ከሚገኘው ቤተ መንግሥት ወደ አዲስ አበባ እንደተወሰዱ ዘገባዎች አመልክተዋል።
ከቅዳሜ አንስቶ በጂጂጋ እና በክልሉ ሌሎች ከተሞች የተከሰተውን አለመረጋጋት ተከትሎ የሃገር መከላከያ ሠራዊት እና የፌደራል ፖሊስ ወደ ክልሉ ጣልቃ ገብቶ አካባቢውን ተቆጣጥሯል።
መከላከያ ወደ ሶማሌ ክልል ጣልቃ የገባው የአብዲ ኢሌ ታጣቂዎች ሰላማዊ ሰዎችን መግደል በመጀመራቸውና በጅግጅጋ ያለው አለመረጋጋት ከቁጥጥር ወጭ በመሆኑ ነው።
በጅግጅጋ ሰሞኑን በነበረ ጥቃት ከ 30 በላይ ሰዎች ሲገደሉ በሺህዎች የሚቆጠሩ ደግሞ ከአካባቢያቸው ተፈናቅለዋል።
አብዲ ኢሌ የክልሉን ምክር ቤት ሰብስቦ የኢትዮጵያን ሶማሌ ለመገንጠል ሲንቀሳቀስ እንደነበር የኮሚንኬሽን ጽሕፈት ቤት ሚንስትሩ አቶ አሕመድ ሽዴ መግለጻቸውም ይታወሳል።
መከላከያ ወደ ጅግጅጋ ከገባ በኋላ ከአብዲ ኢሌ ጋር ድርድር ተካሂዶ ስልጣን ለመልቀቅ መስማማቱ ተነግሯል።
በአብዲ ኢሌ ምትክ ታዲያ የሶማሌ ክልል ፋይናንስ እና ኢኮኖሚ ልማት ቢሮ ሃላፊ የነበሩት አህመድ አብዲ ሞሃመድ የክልሉ ጊዚያዊ ፕሬዝዳንት ሆነው ተሹመዋል።
አዲሱ የሶማሌ ክልል ጊዚያዊ ርእሰ መስተዳደር አህመድ አብዲ ሞሃመድ ከቢቢሲ ሶማልኛ ጋር ባደረጉት ቆይታ የቀድሞ ፕሬዚዳንት ስልጣናቸውን አስረክበው በሰላም የስልጣን ሽግግር መካሄዱን ገልጸዋል።
የቀድሞው ፕሬዝዳንት ሰላማዊ በሆነ ሁኔታ ጂጂጋ በሚገኘው መኖሪያ ቤታቸው ውስጥ ይገኛሉ ሲባል ቢቆይም ዘግይቶ በወጣ መረጃ ግን አብዲ ኢሌ በመከላከያ ሰራዊት በቁጥጥር ስር መሆናቸው ተነግሯል።
ከአብዲ ኢሌ ጋር ቁልፍ የሶማሌ ልዩ ፖሊስ አመራር አባላት ጭምር መታሰራቸው ታወቋል።