ጂጂጋ በመረጋጋት ላይ ናት ተባለ

(ኢሳት ዲሲ–ነሐሴ 1/2010)ጂጂጋ የገባው የመከላከያ ሰራዊት ከተማዋን በማረጋጋት ላይ መሆኑ ተገለጸ።

ላለፉት ሶስት ቀናት በቀውስ ውስጥ የቆየችው ጂጂጋ በአንጻራዊ ሁኔታ መረጋጋት እንደሚታይባት የደረሰን መረጃ አመልክቷል።

አልፎ አልፎ የተኩስ ድምጽ እንደሚሰማ ኢሳት ያነጋገራቸውና በቤተክርስቲያን ተጠልለው የሚገኙ ነዋሪዎች ገልጸዋ።

መከላከያ ሰራዊቱ ከተማዋን ከተቆጣጠረ በኋላ ግን መጠነኛ ለውጥ እያየን ነው ብለዋል።

በተለያዩ የከተማዋ ክፍሎች አሁንም ተደብቀው ያሉ ነዋሪዎች ሁኔታ እንደሚያሳስባቸው ገልጸዋል።

በድሬዳዋም ዛሬ አንጻራዊ መረጋጋት መስፈኑን ለማወቅ ተችሏል። ትላንት የተገደሉ 5 የጅቡቲ ዜጎችን አስክሬን የጅቡቲ መንግስት መውሰዱን የደረሰን መረጃ አመልክቷል።

ባለፉት ሶስት ቀናት ከ60 በላይ ሰዎች እንደተገደሉ ታውቋል።

በሺዎች የሚቆጠሩ የጂጂጋ ነዋሪዎች ቤት ንብረታቸውን አጥተው በቤተክርስቲያን ተሸሽገዋል።

ከቅዳሜ ጀምሮ በተፈጸመው ጥቃት በከተማዋ የሚገኙ የንግድ ተቋማት ከፍተኛ ዝርፊያ የተፈጸመባቸው ሲሆን በእሳት የጋዩ እንዳሉም ተገልጿል።

ከ10በላይ አብያተክርስቲያናት ሲቃጠሉ 3 ካህናትና አገልጋዮች መገደላቸውም ተዘግቧል።

በአብዲ ዒሌ የተደራጁት ሄጎ የተሰኙት ወጣቶችና የልዩ ሃይል አባላት የሚፈጽሙት ጥቃት በመሸሽ ከቤተክርስቲያን የተሸሸጉት በሺዎች የሚቆጠሩ ነዋሪዎች ጥቃት ተሰንዝሮባቸው 4 ወጣቶች መገደላቸውም ታውቋል።

ለሶስት ቀናት በከፍተኛ ስጋት የቆየው የጂጂጋ ነዋሪ ከትላንት ቀትር በኋላ አንስቶ አንጻራዊ ሰላም ማግኘቱን ነው የደረሰን መረጃ የሚያመለክተው።

ትላንት ወደ ጂጂጋ የገባው የመከላከያ ሰራዊት ከሶማሌ ክልል ልዩ ሃይል መጠነኛ የተኩስ ልውውጥ ከገጠመው በኋላ ሙሉ በሙሉ ከተማዋን የተቆጣጠረ መሆኑን መረጃዎች ያለመክታሉ።

ኢሳት ያነጋገራቸው ነዋሪዎች እንደሚሉት ካለፉት ሶስት ቀናት ይልቅ ዛሬ መረጋጋት ይታያል።

አልፎ አልፎ የተኩስ ድምጽ እንደሚሰማ የገለጹት ነዋሪዎች ስጋቱ መሉ በሙሉ ባይቀረፍም ከመከላከያ ሰራዊቱ መግባት በኋላ አንጻራዊ ሰላም ሰፍኗል።

ሆኖም ተደብቀው የሚገኙ በርካታ ነዋሪዎች እንዳሉና የማፈላለጉ ስራ እንዲከናወን ጠይቀዋል።

አሁንም ያለስጋት በከተማዋ ልንቀሳቀስ አልቻልንም ብለዋል በቤተክርስቲያን የተሸሸጉ ነዋሪዎች።

መከላከያ ሰራዊቱ መግባቱን ተከትሎም የልዩ ሃይሉ ከተማዋን ለቆ መውጣቱንም የሚገልጹ መረጃዎች ለኢሳት ደርሰዋል።

በሌላ በኩል የበቀል እርምጃ ይወሰድብናል በሚል የሶማሌ ክልል ተወላጆች ስጋት እንዳደረባቸው የኢሳት ምንጮች ገልጸዋል።

የተፈጠረው ችግር የህዝብ ለህዝብ ባለመሆኑ የእርስ በእርስ ጥቃት ከመሰንዘር እንዲታቀብ ለህዝቡ መልዕክት ተላልፏል።

በተያያዘ ዜናም በድሬዳዋ ያለው አለመረጋጋትም እየሰከነ መሆኑን ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

በድሬዳዋ በተፈጸመው ጥቃት ከ10 በላይ ሰዎች የተገደሉ ሲሆን 5ቱ የጅቡቲ ዜጎች መሆናቸው ታውቋል።

በዛሬው ዕለት የጅቡቲ መንግስት የተገደሉ ዜጎቹን አስክሬን መውሰዱን የደረሰን መረጃ አመልክቷል።