(ኢሳት ሐምሌ 30/2010)በጅግጅጋ የመከላከያ ሰራዊት ከተማዋን ተቆጣጠረ
ካለፈው ቅዳሜ ጀምሮ የአብዲ ኢሌ ልዩ ሃይል አባላት እና እርሱ ያደራጃቸው ወጣቶች በክልሉ በሚኖሩ የሌሎች ብሄር ተወላጆች ላይ ጥቃት በመፈጸም፣ የበርካታ ዜጎች ህይወት እንዲጠፋ አድርገዋል። ከ7 ያላነሱ አብያተ ክርስቲያናት ተቃጥለዋል። የሌሎች ብሄሮች እና አብዲ ኢሌን ይቃወማሉ የተባሉ የኢትዮ-ሶማሊ ተወላጆች ንብረት ተዘርፏል፤ ከፍተኛ ሃብትና ንብረትም ወድሟል። በርካታ ዜጎች ሚካኤል ቤተከርስቲያን ውስጥ ተጠልለው ያለፉትን 2 ቀናት በርሃብና ጥም አሳልፈዋል። ቅዳሜ እለት መከለከያ ሰራዊት የአብዲ ኢሌን መኖሪያ ግቢ ተቆጣጥሮ የነበረ ቢሆንም፣ ምክንያቱ ባልታወቀ ሁኔታ በመውጣቱ ህዝቡ ስጋቱን ሲገልጽ ቆይቷል። ጥቃቱ እስከዛሬ በመቀጠሉ ዜጎች በአዲስ አበባ የሚኖሩ ዜጎች ወደ አደባባይ በመውጣት መንግስት መልስ እንዲሰጥ ጥያቄ አቅርበዋል።
ቀን ላይ የአብዲ ኢሌ ልዩ ሃይል አባላት ከ4 ያላነሱ ሰዎችን መግደላቸውን ተከትሎ፣ ከሰዓት በሁዋላ የመከላከያ ሰራዊት በጭናክሰን በኩል በመግባት በልዩ ሃይሉ ላይ ጥቃት በመሰንዘር ከተማውን ተቆጣጥሯል። ነዋሪዎች ከፍተኛ ተኩስ ይሰማ እንደነበር ገልጸዋል። መከላከያ ወደ ከተማው መግባቱን ተከትሎም ህዝቡ ደስታውን በአደባባይ ሲገልጽ እንደነበር ያነጋገርናቸው ሰዎች ገልጸዋል።
በሌላ በኩል
በትናንትናው ዕለት በድሬዳዋ ከተማ 09 ቀበሌ ተብሎ በሚጠራው አከባቢ በተከሰተው ግጭት አራቱ ታዳጊ ህጻናትን ጨምሮ የአስር ሰዎች ህይወት ማለፉን የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ፖሊስ ኮሚሽን ገልጿል።
በርካታ ቤቶች መቃጠላቸውን እንዲሁም ከፍተኛ ንብረት መውደሙን ፖሊስ አስታውቋል።