የሶማሊያው ፕሬዚዳንት ከነገ ጀምሮ ኤርትራን ይጎበኛሉ።
( ኢሳት ዜና ሃምሌ 20 ቀን 2010 ዓ/ም ) በአፍሪቃ ቀንድ በቅርቡ እየተስተዋሉ ያሉ የፖለቲካ አሰላለፍና የዲፕሎማሲ ለውጦችን ተከትሎ የሶማሊያው ፕሬዚዳንት መሀመድ አብዱላሂ ፎርማጆ ከነገ ጀምሮ በኤርትራ የሦስት ቀናት የሥራ ጉብኝት ያደርጋሉ።
የኤርታራው ማስታወቂያ ሚኒስትር በትዊተር ገጻቸው እንደገለጹት የሶማሊያ ሪፐብሊክ መሪ የሆኑት ፕሬዚዳንት ፎርማጆ ኤርትራን የሚጎበኙት፣ በፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ግብዣ መሰረት ነው። በዚህም መሰረት ፣ፕሬዚዳንት ሙሀመድ አብዱላሂ ፎርማጆና የል ኡካን ቡድናቸው ነገ ማለዳ አስመራ ይገባሉ ተብሎ ይጠበቃል። እንደ ቢቢሲ ዘገባ፣ ይህ የሶማሊያ ፕሬዚዳንት የኤርትራ ጉብኝት በኢትዮጵያ እና በኤርትራ መካከል ዳግም ሰላም መፈጠሩን ተከትሎ የተደረገ ነው።
ከሳምንታት በፊት ዶክተር አብይ አህመድ ወደ ሞቃዲሾ በማቅናት ከፕሬዚዳንት ፎርማጆ ጋር መነጋገራቸው አይዘነጋም። በመንግስታቱ ድርጅት የሚደገፈው እና ለረዥም ጊዜ ከኢትዮጵያ ጋር ወዳጅ ሆኖ የቆዬው የሶማሊያ መንግስት ከኤርትራ ጋር መልካም ግንኙነት አልነበረውም።
ኤርትራ አልሸባብን እንደምትረዳ በቀረበባት ክስ ሳቢያ እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር ከ2009 ጀምሮ በመንግስታቱ ድርጅት ማዕቀብ ተጥሎባት ነበር። አስመራ ግን የቀረበባት ክስ ስታስተባብል ቆይታለች።
በመሆኑም በአሁኑ ወቅት በኤርትራ ላይ ተጥሎ የቆዬው ማዕቀብ እንዲነሳ ጥሪ እየቀረበ ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ በኤርትራ ጉብኝት ማግስት አዲስ አበባ ለመጡት የመንግስታቱ ድርጅት ዋና ጸሀፊ በኤርትራ ላይ የተጣለው ማዕቀብ እንዲነሳ ጥሪ ማቅረባቸው ይታወሳል።
ልክ እንደ ኢትዮጵያ ሁሉ-ከኤርትራ ጋር ላለፉት 20 ዓመታ ተኳርፉ የቆየችው ጅቡቲም ከጥቂት ቀናት በፊት ከአስመራ ጋር እርቅ እንደምትፈልግ እና የእርቅ መንገዱ እንዲመቻችላት መጠየቋን ሬውተርስ የዜና አገልግሎት አስነብቧል።
የጅቡቲው ፕሬዚዳንት የእርቅ ጥያቄውን ያቀረቡት ጄኔቫ በሚገኙት የመንግስታቱ ድርጅት የጁቡቲ አምባሳደር አማካይነት ነው።