(ኢሳት ዲሲ–ሐምሌ 20/2010) ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ከአርበኞች ግንቦት ሰባት ሊቀመንበር ከፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ጋር ተወያዩ።
የአርበኞች ግንቦት 7 ዋና ጸሃፊ አቶ አንዳርጋቸው ጽጌም ትላንት ምሽት አሜሪካ ገብተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዛሬ ከፖለቲካ ፓርቲ መሪዎች ጋር እንደሚወያዩም ከወጣው መርሃ ግብር መረዳት ተችሏል።
ትላንት ሐሙስ ማለዳ ዋሽንግተን ዲሲ የደረሱት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ ረፋድ ላይ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን አባቶች የዕርቅ ሒደት ላይ ተሳትፈዋል።
ከቀትር በኋላም ከፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ጋር በግል መገናኘታቸው ታውቋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድና የአርበኞች ግንቦት ሰባት ሊቀመንበር ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ በምን ጉዳይ ላይ እንደተነጋገሩ የታወቀ ነገር የለም።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዛሬ አርበኞች ግንቦት ሰባትን ጨምሮ የፖለቲካ ፓርቲ ድርጅት መሪዎች ጋር እንደሚነጋገሩም ከወጣው መርሃ ግብር መረዳት ተችሏል።
ይህ በእንዲህ እንዳለም የአርበኞች ግንቦት 7 ዋና ጸሃፊ አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ከጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ ጋር ለመገናኘትና በታሰሩበትም ወቅት ከጎናቸው የነበሩ ኢትዮጵያውያንን ለማመስገን ትላንት ምሽት ዋሽንግተን ዲሲ ገብተዋል።
አቶ አንዳርጋቸው እንደሚመጡ በተለያየ መንገድ የሰሙ መዳጅና ደጋፊዎቻቸውም በዋሽንግተን ዳላስ አውሮፕላን ማረፊያ አቀባበል አድርገውላቸዋል።
ዛሬ ከቀትር በኋላ ከፖለቲካ ፓርቲ መሪዎች ጋር ለመወያየት መርሃ ግብር የያዙት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ ምሽት ላይ ከባለሙያዎችና ከንግዱ ማህበረሰብ አባላት ጋር ይወያያሉ።
ከዚህም ሌላ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በውሏቸው ከሙስሊሙ ማህበረሰብ ጋር እንደሚመክሩም ታውቋል።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ፓትሪያርክ ብጹእ ወቅዱስ አቡነ መርቆሪዎስ ጋር ነገ እንደሚያገኙም ተመልክቷል።
እስከ 40ሺ ሰዎች ይታደሙበታል የተባለው ትልቁ ሕዝባዊ ስብሰባ ነገ በዋሽንግተን ዲሲ ሰአት አቆጣጠር ከቀኑ 1 ፒኤም በኢትዮጵያ ሰአት አቆጣጠር ደግሞ ከምሽቱ 2 ሰአት ላይ ይጀምራል።
በዚህ ዝግጅት ላይ ለሚታደሙ ተሳታፊዎች አዳራሹ ከጠዋቱ 9 ኤ ኤም ጀምሮ ክፍት እንደሚሆን ታውቋል።
በዚህ ዕለት ምሽት ከተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች ከተውጣጡ 1 ሺ 500 ከሚሆኑ እንግዶች ጋር የሚወያዩት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ እሁድ ከዋሽንግተን ዲሲ 3ሺ 680 ኪሎ ሜትር ወደ ሚርቀው ሎስ አንጀለስ የ5 ሰአት ያህል በረራ ካደረጉ በኋላ በሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን በሚታደሙበት ስብሰባ ላይ ይሳተፋሉ ተብሏል።
በሎስ አንጀለስ ቆይታቸውም ከተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች ጋር ከተወያዩ በኋላ ሰኞ ወደ ማዕከላዊው የአሜሪካ ግዛት ከተጓዙ በኋላ በሚኒያ ፖሊስ ከተማ ተመሳሳይ ሕዝባዊ ስብሰባ ያደርጋሉ።
ከተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች ጋር ውይይታቸውን ካጠናቀቁም በኋላ ማክሰኞ ወደ ኢትዮጵያ እንደሚመለሱ ታውቋል።
ሰኞ በሚኒያ ፖሊስ በሚደረገው ስብሰባ የኦሮሚያ ክልል ፕሬዝዳንት አቶ ለማ መገርሳም ከኦሮሞ ማህበረሰብ ጋር ይወያያሉ ተብሎ ይጠበቃል።
የአማራ ክልል ፕሬዝዳንት አቶ ገዱ አንዳርጋቸውም ሰሞኑን አሜሪካ ይገባሉ ተብሎ እየተጠበቀ ነው።