ፓትሪያርክ አቡነ መርቆሪዎስ በነሐሴ መጨረሻ ወደ ሃገራቸው ሊመለሱ ነው

(ኢሳት ዲሲ–ሐምሌ 20/2010) የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ፓትሪያርክ አቡነ መርቆሪዎስ በነሐሴ መጨረሻ ወደ ሃገራቸው እንደሚመለሱ ምንጮች ገለጹ።

በሁለቱ ሲኖዶሶች መካከል ከሩብ ክፍለ ዘመን በላይ የቀጠለው ውዝግብ ፍጻሜ ማግኘቱም ይፋ ሆኗል።

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ በተገኙበት በአሜሪካ ዋሽንግተን ዲሲ ዋተር ጌት ሆቴል ውስጥ በተካሄደው ስነስርአትም  አቡነ መርቆሪዎስ ከነሙሉ ክብራቸውና ማዕረጋቸው ወደ ኢትዮጵያ ተመልሰው በመንበራቸው እንዲቀመጡ ተወስኗል።

በብጹዕ አቡነ አብርሃም በተነበበውና በሁለቱም ወገን አባቶች በሙሉ ድምጽ በተወሰነው መሰረት አቡነ መርቆሪዎስ ወደ ሃገራችው ከነክብራቸው በመንበራቸው ላይ እንዲመለሱ ተወስኗል።

አቡነ ማቲያስም የአስተዳደር ስራዎችን በበላይ እንዲመሩና በማዕረጋቸው እየተጠሩ እንዲቀጥሉም ከውሳኔ ላይ ተደርሷል።

ከእንግዲህ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ያላት አንድ ሲኖዶስ ብቻ መሆኑም በይፋ ታውጇል።

በሁለቱ ወገን የተጣለው ውግዘት እንደተነሳ በተነገረበት በዚህ ታሪካዊ ስነስርአት ላይ በሁለቱም ወገን ከልዩነቱ በኋላ የተሾሙ አባቶች በማዕረጋቸውና በመጠሪያቸው የቅዱስ ሲኖዶሱ አባል ሆነው እንደሚቀጥሉም ተመልክቷል።

የሩብ ክፍለ ዘመን ቀውስና ውዝግብ መቋጫ ባገኘበት ልዩ ስነስርአት ላይ የተገኙት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ በዕርቁ መደሰታቸውን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያዊ ነኝ የሚል ሁሉ የሚደሰትበት ትልቅ ቀን ነው ብለዋል።

በዚህ እርቅ የኢትዮጵያ ሙስሊሞችም እንኳን ደስ አላችሁሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

ቤተክርስቲያኗ በፈተና ውስጥ ባለፈችበት ወቅት በዝምታ ነገሮችን ባዩ ሁሉ መገረማቸውን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል።

መንግስትም እስከዛሬ የሚገባውን ተግባር ባለመፈጸሙ በይፋ ይቅርታ ጠይቀዋል።

የጥላቻው ግንብ ዋነኛው ምሰሶ ዛሬ ተንዷል ያሉት ዶክተር አብይ አህመድ ግንቡ መፍረስ ጀመረ እንጂ አልተጠናቀቀምና በጸሎታችሁ አስቡን፣በሃገሪቱ የእርቅ  ሒደት ሁሉ በግንባር ቀደምትነት ተሳተፉ ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ አንድ ብትሆን ኖሮ ከራሳችን አልፈን ለአካባቢው ሰላም እንተርፍ ነበር ሲሉ መልዕክት አስተላልፈዋል።

ይህ ዛሬ በባዕድ ሃገር የተካሄደው ስነስርአት በሃገራችን በሚሊኒየም አዳራሽ በደማቅ ዝግጅት ይበሰራ ሲሉም ቃል ገብተዋል።

ላለፉት 25 አመታት በስደት ላይ የሚገኙት ፓትሪያርክ ብጹእ ወቅዱስ አቡነ መርቆሪዎስ በነሐሴ ወር መጨረሻ ኢትዮጵያ እንደሚመለሱና በመንበራቸው ላይ እንደሚቀመጡም የቅርብ ምንጮች ገልጸዋል።