በሳውላ ለዶ/ር አብይ አህመድ ድጋፍ ሲያስተባብሩ የነበሩ ሰዎች ጥቃት እየደረሰባቸው ነው
( ኢሳት ዜና ሃምሌ 13 ቀን 2010 ዓ/ም ) በጎፋ ሳውላ የተካሄደውን የድጋፍ ሰልፍ ተከትሎ ፣ ሰልፉን አስተባብራችሁዋል የተባሉ ሰዎች እየተደበደቡ ታስረዋል። በሰልፉ ዋዜማ እለት አንድ እናት እስከ ልጃቸው የተደበደቡ ሲሆን፣ ከሰልፉ በሁዋላ ደግሞ በርካታ ወጣቶች በባለስልጣናት ድብደባ ደርሶባቸዋል።
የአካባቢው ነዋሪዎች እንደገለጹት 5 ሰዎች ፖሊስ ጣቢያ ታስረው ቤተሰብ እንዳይጠይቁዋቸው የተደረገ ሲሆን፣ ሌሎች ወጣቶች ደግሞ ተደብድበው ሆስፒታል ገብተዋል። ሌሎች ወጣቶች ደግሞ ተሰደው አርባ ምንጭ መግባታቸው ታውቋል። ጥቃት የተፈጸመባቸው የወረዳው ባለስልጣናት ለምን ከስልጣን ይውረዱ አላችሁ፣ ለምን የቀን ጅብ አላችሁ በሚል እንደሆነ ነዋሪዎች ገልጸዋል።
ለዶ/ር አብይ ድጋፍ ያሰባሰቡ አንዳንድ የመንግስት ሰራተኞችም ከስራ እየተባረሩ መሆኑን ለኢሳት በሚልኳቸው መርጃዎች እየገለጹ ይገኛሉ።