በአማራ ክልል በአሁኑ ወቅት በስውር ችግር የመፍጠር አቅም ያለው አካል የለም

(ኢሳት ዲሲ–ሐምሌ 13/2010) በአማራ ክልል በአሁኑ ወቅት ሌላ ሃይል ጣልቃ ገብቶ በሃይል ወይንም በስውር ችግር የመፍጠር አቅም እንደሌለው ርዕሰ መስተዳድሩ አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ገለጹ።

ርዕሰ መስተዳድሩ ሁሉም አቅም በራሳችን እጅ ስላለ የሕግ የበላይነትን የማስከበር ስራው በኛ ብቻ ይወሰናል ሲሉ ተናግረዋል።

ከዚህ በፊት በነበሩ ሁኔታዎች የሰብአዊ መብት ጥሰቶችና ሌሎች ችግሮች ከክልሉ መንግስት ቁጥጥር ውጭ ነበሩ ብለዋል።

በአማራ ክልል ችግሮች ቢፈጠሩ እንኳን በራሳቸው እንጂ በሌሎች የምናሳብብባቸው አይደሉም ሲሉ ነው ርዕሰ መስተዳድሩ አቶ ገዱ አንዳርጋቸው የተናገሩት።

አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ ሌላ አካል መጥቶ ጉዳት ማድረስ አይችልም፣ስለዚህ በሌላ አካል የምናመካኝበት ጊዜ አይደለም ብለዋል።

እንደ አቶ ገዱ ገለጻ ከዚህ በፊት ችግሮች ነበሩ።እነዛ የተፈጠሩ የሰብአዊ መብት ጥሰቶችና ችግሮች ከክልሉ መንግስት ቁጥር ውጭ ነበሩ ሲሉ ነው የገለጹት።

በአሁኑ ወቅት ግን በአማራ ክልል ላይ ሌላ ሃይል ጣልቃ ገብቶ በሃይል ወይም በስውር ችግር የመፍጠር ተግባር በእጅጉ ተዳክሟል ብለዋል።

እናም ሁሉም አቅም በእጃችን ላይ ስላለ ሰላምን ወይንም የሕግ የበላይነትን የማስከበር ስራው በኛ ላይ ይወሰናል ነው ያሉት።

የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው በምስጋናና ድጋፍ ሰልፎች ላይ ሃሳብን ስለመግለጽ ነጻነትም ተናግረዋል።

አቶ ገዱ በሰልፎች ላይ የሕብረተሰቡን የለውጥ ፍላጎት አይተናል፣ሕዝቡም ያልፈለገውን ኮንኗል ብለዋል።

ይህም ሃሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት ሕገመንግስታዊ በመሆኑ መብቱ እንደሆነ ነው የገለጹት።

ምልክት የሌለበትን ባንዲራ መያዙና ፍላጎቱን መግለጽም መብቱ እንጂ ሕገወጥ የሚያስብል አይደለም ብለዋል።

ሕብረተሰቡ ይዞት የመጣውን ሰንደቅ አላማ ለምን ይዞ ወጣ በማለት ሕገ ወጥ ነው ማለት አግባብ አይደለም ብለዋል።

ይልቁንስ ጉዳዩን መመርመርና የሕዝቡን ፍላጎት መስማት ይገባልም ነው ያሉት።

የአሮጌው ዘመን ቁማርተኞች በሚል ርዕሰ መስተዳድር ገዱ አንዳርጋቸው ከዚህ ቀደም የገለጹበትን ሁኔታ ተጠይቀውም ለውጡን ለማደናቀፍ የሚፈልጉትንና በኢሕአዴግ ስራ አስፈጻሚ የተቀመጠውን አቅጣጫ ለመቀልበስ የሚሞክሩትን ለማውገዝ እንደሆነ ገልጸዋል።