(ኢሳት ዲሲ–ሐምሌ 10/2010) የአዲስ አበባ ከንቲባ የነበሩትን አቶ ድሪባ ኩማን የሚተኩ ሹም በከተማዋ አስተዳደር ምክር ቤት ተሰየመ።
በምክትል ከንቲባ ማዕረግ አዲስ አበባን እንዲያስተዳድሩ በከተማዋ አስተዳደር የተሾሙት ኢንጂነር ታከለ ኡማ ናቸው።
የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ የነበሩት አቶ ድሪባ ኩማ በቅርቡ አምባሳደር ሆነው መሾማቸው ይታወሳል።
የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት ዛሬ ባካሄደው ልዩ ስብሰባ ኢንጂነር ታከለ ኡማን ምክትል ከንቲባ በማድረግ ሾሟል።
ኢንጂነር ታከለ ከንቲባ ሆነው ያልተሾሙት የምክር ቤት አባል ስላልሆኑ ነው ተብሏል።
እናም ምክትል ከንቲባው አቶ ድሪባ ኩማን ተክተው እንደሚሰሩ ነው የተገለጸው።
በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ደንብ መሰረት የምክር ቤት አባል ያልሆነ ሰው ከንቲባ ሆኖ ሊሾም አይችልም።
ኢንጂነር ታከለ ኡማ ከዚህ ቀደም የሱሉልታ ማዘጋጃ ቤት ሃላፊ እንዲሁም የሆለታ ከተማ ከንቲባ ሆነው አገልግለዋል።
የአዲስ አበባ ምክር ቤት በምርጫ ከተሰየመ አምስት አመት ቢሆነውም አሁንም ስልጣን ላይ ይገኛል።
አገልግሎቱን ያጠናቀቀው የአዲስ አበባ ምክር ቤት አሁንም በስራ ላይ የሚገኘው በወቅቱ መካሄድ የነበረበት የክልልና የአካባቢ ምርጫ በጸጥታ ችግር ምክንያት ሕገ መንግስቱ ተጥሶ በመራዘሙ ነው።
ይህ ከሆነ በኋላም ፓርላማው የምክር ቤቱን ስልጣን የማራዘሚያ አዋጅ በማውጣት ለአንድ አመት እንዲራዘም አድርጎታል።
ለአዲስ አበባ ምክር ቤት ከንቲባነት የብአዴኑ ዶክተር አምባቸው መኮንን ታጭተዋል ተብሎ ሲነገር ነበር።
ይህም በመሆኑ አዲስ አበባ በኦሮሚያ ክልል የምትገኝ በመሆኗ እንዴት ከኦሕዴድ ይወጣል በሚል ጭቅጭቅ የፈጠረ ጉዳይ ሆኖም ቆይቷል።
በመጨረሻም ኢንጂነር ታከለ ኡማን ከኦህዴድ በመምረጥ ምክትል ከንቲባ አድርጎ ሾሟል።
የአዲስ አበባ ጉዳይ ከኦሮሚያ ጥቅም አንጻር ልዩ መብት ያስፈልጋል በመባሉም አሁንም በዚህ ዙሪያ ያልተፈታ ችግር ተደርጎ ይወሰዳል።
ብዙዎች እንደሚሉት አዲስ አበባ የሁሉም ብሔረሰቦች መቀመጫና የፌደራል ከተማ በመሆኗ ልዩ ጥቅም የሚለውን ሃሳብ የሚቃወሙ ብዙ ናቸው።