ዐቃቤ ሕግ በአርበኞች ግንቦት 7 የተከሰሱት ክስ እንዳይቋረጥ ጠየቀ

ዐቃቤ ሕግ በአርበኞች ግንቦት 7 የተከሰሱት ክስ እንዳይቋረጥ ጠየቀ
( ኢሳት ዜና ሃምሌ 10 ቀን 2010 ዓ/ም ) የፌደራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ የአርበኞች ግንቦት 7 ስም ከአሸባሪነት ዝርዝር ቢነሳም ፣ በስሙ የተከሰሰሱትና በእስር ላይ የሚገኙት አባሎች ክሳቸው መነሳት የለበትም ሲል መከራከሩን ጋዜጠኛ ጌታቸው ሽፈራው ዘግቧል። ሐምሌ 10/2010 ዓም በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 19ኛ ወንጀል ችሎት በአርበኞች ግንቦት 7 ስም በእነ ሚፍታህ ሸሕ ሱሩር ክስ መዝገብ ከተከሰሱት 77 ግለሰቦች መካከል ያልተፈቱት 46 ተከሳሾች የቀረቡ ሲሆን፣ ዐቃቤ ሕግ ክሳቸው መቋረጥ የለበትም ሲል ተከራክሯል።
ፍርድ ቤቱ የተወካዮች ምክር ቤት አርበኞች ግንቦት 7 ከፀረ ሽብር አዋጁ ስሙ እንዲነሳ ካደረገ በኋላ የሽብር ክሶች እንዲቋረጡ “የስራ መመርያ” ይተላለፋል ብሎ እየጠበቀ እንደነበር፣ ነገር ግን እንዳልደረሰው ገልፆአል።
ተከሳሾቹ የተከሰሱበት ድርጅት ስም ከፀረ ሽብር አዋጁ መነሳቱን በመግለፅ መፈታት እንዳለባቸው ቢገልፁም፣ ዐቃቤ ሕግ “ድርጊቱ የተፈፀመው የድርጅቱ ስም ከፀረ ሽብር አዋጁ ከመነሳቱ በፊት ነው። የድርጅቱ ስም ከአዋጁ በመነሳቱ ብቻ ክሳቸው ሊቋረጥ አይገባም። ክርክሩ መቀጠል አለበት።” ሲል ከፀረ ሽብር አዋጁ ስማቸው በተነሳለቸው ድርጅቶች ስም የተመሰረተው የሽብር ክስ መቋረጥ የለበትም ሲል ተከራክሯል።
ከሶስት ቀን በፊት ከዐቃቤ ሕግ መስርያ ቤት የተወከለ ሰው ቂሊንጦ እስር ቤት እስረኞችን ባወያየበት ወቅት፣ በሽብር ተከስሰው ያልተፈቱት አቤቱታ ሲያቀርቡ “በዚህ ክስ ተከስሶ እስካሁን እስር ቤት ያለ ሰው ስለመኖሩ አናውቅም” የሚል መልስ እንደሰጣቸው ተከሳሾች ለፍርድ ቤቱ መግለጻቸውን ጋዜጠኛ ጌታቸው በፌስቡክ ገጹ አስነብቧል።
ፍርድ ቤቱም “የድርጅቱ ስም ከፀረ ሽብር አዋጁ መነሳቱን ብንሰማም፣ የስራ መመርያ አልደረሰኝም” በሚል ለሀምሌ 17/2010 ዓም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።