(ኢሳት ዲሲ–ሐምሌ 10/2010) በሕዝባዊ ወያኔ ሃርነት ትግራይ/ሕወሃት /ሰዎች ላለፉት 27 አመታት በቋሚነት ተይዞ የነበረው በቻይና የኢትዮጵያ አምባሳደርነት ስፍራ ለሌላ ኢትዮጵያዊ ሊሰጥ መሆኑን ምንጮች ገለጹ።
በአሁኑ ወቅት በቻይና አምባሳደር ሆነው የሚሰሩት አምባሳደር ብርሃነ ገብረክርስቶስ ወደ ሃገር ቤት መጠራታቸውም ታውቋል።
የሕዝባዊ ወያኔ ሃርነት ትግራይ መሪዎች በግልና በኤፈርት ስም ከሃገር የዘረፉትን ገንዘብ ካሸሹባቸው ሃገራት በግንባር ቀደምትነት በምትጠቀሰው ቻይና ለአንድ አመት ያህል በአምባሳደርነት ያገለገሉት አምባሳደር ብርሃነ ገብረ ክርስቶስ የተጠሩበት ምክንያት ግን አልተገለጸም።
ሆኖም በእሳቸው ምትክ በቅርቡ አምባሳደር እንደሚሾም እየተጠበቀ ሲሆን ለመጀመሪያ ጊዜ የሕወሃት አባል ያልሆነ ሰው በቻይና የኢትዮጵያ አምባሳደር እንደሚሆን የኢሳት ምንጮች ገልጸዋል።
ላለፉት 27 አመታት በቻይና በአምባሳደርነት ያገለገሉ የሕወሃት አባላት አምባሳደር አዲስ አለም ባሌማ፣አምባሳደር ዶክተር ሃይለኪሮስ ገሰሰ፣አምባሳደር ስዩም መስፍንና አምባሳደር ብርሃነ ገብረክርስቶስ ናቸው።