(ኢሳት ዲሲ–ሐምሌ 6/2010) በቂሊንጦ እስር ቤት የእሳት ቃጠሎ መድረሱ ተነገረ።
በእስር ቤቱ የእንፈታ ጥያቄ ያቀረቡ ዜጎች ላይ አስለቃሽ ጋዝ ሲተኮስ እንደነበርና የቦምብ ፍንዳታም መሰማቱ ተነግሯል።
እስረኞቹን ለመጠየቅ የመጡ ሰዎች በፖሊስ እንደተደበደቡ ለማወቅ ተችሏል።
በቂሊንጦ እስር ቤት እስረኞች የእንፈታ ጥያቄ አቅርበው ግጭት መቀስቀሱ ተሰምቷል።
እስረኞቹ የኦነግና የአርበኞች ግንቦት ሰባት አባላት በሚል ታስረው ከነበሩት መካከል መሆናቸውም ታውቋል።
ድሃ በመሆናችንና ታዋቂ ባለመሆናችን ከእስር አለመፈታታችን አግባብ አይደለም ሲሉ ታራሚዎቹ ተቃውሞ አሰምተዋል።
የእስረኞቹን ተቃውሞ ተከትሎ በግቢው ውስጥ አስለቃሽ ጭስ መተኮሱንና የእሳት ቃጠሎ መከሰቱ ተነግሯል።
በቂሊንጦ የእሳት አደጋ መከላከያ ተሽከርካሪዎች መሰማራታቸውም ነው የተገለጸው።
በእስርቤቱ የቦምብ ፍንዳታ ድምጽ እንደተሰማ ቢነገርም ስለደረሰው ጉዳት ግን የታወቀ ነገር የለም።
የእስረኞቹን ጩኽት የሰሙት የታሳሪ ቤተሰቦች በአካባቢው ጋዜጠኞችም ሲዋከቡ የሚያሳዩ በምስል የተደገፉ ማስረጃዎች በማህበራዊ ድረ ገጾች ላይ ተለቀዋል።
በቂሊንጦ እስር ቤት ከዚህ ቀደም በተነሳ የእስረኞች አመጽ ሳቢያ ከ20 በላይ ታራሚዎች በእሳትና በተተኮሰባቸው ጥይት መገደላቸው ይታወሳል።
በዚሁም ምክንያት 38 እስረኞች በግድያና በእሳት ቃጠሎ ወንጀል ተከሰው ፍርድ ቤት ሲመላላሱ እንደነበርም ይታወሳል።
በኋላም ከእስረኞቹ ብዙዎቹ ሲለቀቁ 4 ታራሚዎች ብቻ ፍርዱ እንዲጸናባቸው ተደርጓል።
በሙስና ሰበብ ታስረው የነበሩት የልብ ሃኪሙ ዶክተር ፍቅሩ ማሩም የቃጠሎውን ሴራና ግድያውን አቀነባብረዋል ተብለው ተጨማሪ ክስ ቀርቦባቸው እንደነበር አይዘነጋም።
ዶክተር ፍቅሩ ማሩ በመጨረሻ ክሳቸው ተቋርጦ ከእስር መለቀቃቸው ይታወሳል።