በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ለዶ/ር አብይ አህመድ የሚደረጉ የድጋፍ ሰልፎች ቀጥለዋል
( ኢሳት ዜና ሃምሌ 2 ቀን 2010 ዓ/ም)ባለፈው ቅዳሜ እና እሁድ እንዲሁም ዛሬ ሰኞ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የሚገኙ ኢትዮጵያውያን የዶ/ር አብይ አህመድ አስተዳደር እየወሰደ ያለውን እርምጃ በማድነቅ ድጋፋቸውን ገልጸዋል።
በአርባምንጭ ከተማ ዛሬ በተደረገው የድጋፍ ስልፍ የከተማ ነዋሪዎች አርማ የሌለውን ረጅም ሰንደቅ አለማ በማሰራትና የተለያዩ መፈክሮችን በመያዝ ድጋፋቸውን ሲገልጹ ውለዋል። በክብር እንግድነት የተጋበዙት የሰማያዊ ፓርቲ የአመራር አባል የሆኑት አቶ ደንኤል ሽበሺ እንዲሁም በቅርቡ ከእስር የተፈታው ባንተወሰን አበበና ሌሎችም እንግዲች ንግግሮችን አድርገዋል። የተቃውሞ ሰልፉን በተመለከተ ከአዘጋጆቹ መካከል አንዱ የሆነው ወጣት ኪሩቤል ግርማ፣ ሰልፉ በተሳካ ሁኔታ መጠናቀቁን ተናግሯል።
በሌላ በኩል ደግሞ ትናንት በራያ አላማጣ ለዶ/ር አብይ የተደረገውን የድጋፍ ሰልፍ የትግራይ ክልል የጸጥታ ሃይሎች በጉልበት መበተናቸውን የአካባቢው ነዋሪዎች ተናግረዋል። ወጣቶቹ አርማ የሌለውን ሰንደቃላማ መያዛቸው ያበሳጫቸው የትግራይ ክልል ባለስልጣናት ፣ በወጣቶቹ ላይ ድብደባ እንዲፈጸም በማዘዛቸው በርካታ ወጣቶች በድብደባ ከፍተኛ ጉዳት ደርሶባቸዋል። ቁጥራቸው በውል ያልታወቀ ወጣቶችም ተይዘው ታስረዋል። በራያ አካባቢ ያለው ውጥረት መጨመሩን ተከትሎ በርካታ ቁጥር ያላቸው የክልሉ ወታደሮች አሁንም ቁጥጥር እያደረጉ ሲሆን፣ ወጣቶቹ ግን ሰልፉን በሚቀጥለው ሳምንትም እንደሚያደርጉ እየገለጹ ነው።
ስሜን አትጠቀሱ ያሉት የከተማዋ ነዋሪ፣ ዶ/ር አብይን የሚደገፍ ማንኛውም ሰው በጥይት እንዲመታ የትግራይ ክልል ውሳኔ ማሳለፉን የሚገልጹት የራያ ነዋሪ፣ 9 ወጣቶች ታፍነው መወሰዳቸውን ተናግረዋል። ነዋሪዎች ወጣቶች ያሉበትን ለማፈላለግ ሙከራ ሲያደርጉ፣ በወታደሮች መዋከባቸውን ተናግረዋል።
ተመሳሳይ የድጋፍ ስልፍ በአማራ ክልል በአዊ ዞን ዋና ከተማ እንጅባራ ተካሂዷል። የከተማ ነዋሪዎች ረጅም ሰንደቃላማና የተለያዩ መፈክሮችን በመያዝ ድጋፋቸውን ገልጸዋል።
በዳንግላ ከተማ፣ በሰሜን ወሎ ቆኔ ከተማ እንዲሁም በሰሜን ሸዋ ዞን በአንጾኪያ ገምዛ ወረዳ የድጋፍ ሰልፍ ተካሂዷል።