ወደ አማራ ክልል ሊገቡ የነበሩ 25 ኤፍ አንድ ቦንቦች ተያዙ።

ወደ አማራ ክልል ሊገቡ የነበሩ 25 ኤፍ አንድ ቦንቦች ተያዙ።
( ኢሳት ዜና ሃምሌ 2 ቀን 2010 ዓ/ም)ቦንቡን በመያዝ ጥቃት ለመፈጸም የተንቀሳቀሱት ግለሰቦች ባለፈው ዓመት ከተለያዩ ዩኒቨርስቲዎች የተመረቁ መሆናቸውን የተናገሩ ሲሆን ፤ወጣቶቹ ከተመረቁ በኋላ በስውር በመመልመል አጭር ስልጠና ተሰጥቷቸዋል።
ሰኔ 26 ቀን 2010 ዓም ከአዲስ አበባ ተነስቶ ወደ ደጀን ከተማ በመሄድ በጠቅላይ ሚኒስተር ዶክተር ዐብይ አህመድ የድጋፍ ሰልፍ ላይ በሚሳተፉ ዜጎች ላይ አደጋ ለማድረስ ሲጓዝ የተያዘው ወጣት ዘረሰናይ ወልዱ፣ በደብረ ብርሃን ዩኒቨርስቲ በ2009 ዓም የተመረቀ ሲሆን አጭር ስልጥና ከተሰጠው በኋላ ሶስት መቶ ሽህ ብር ተሰጥቶት የሽብር ጥቃቱን ለማድረስ 16 ኤፍ አንድ ቦንብ በዘንቢል በመያዝ ሲንቀሳቀስ በጥርጣሬ መያዙን የዓይን እማኞች በተለይ ለኢሳት ዘጋቢ ተናግረዋል።
ሌላው ተጠርጣሪ ተሻገር ወልደ ሚካኤል የተያዘው በትላንትናው ሰኔ 27 ቀን 2010 ዓም በእንጅባራ ከተማ ሲሆን በተመሳሳይ ባለፈው ዓመት ከሰመራ ዩኒቨርስቲ የተመረቀ መሆኑን ለደህንነት ሰዎች ገልጿል። በማይጸምሬና ሽረ ውስጥ ትምህርቱን መከታተሉንም ወጣቱ ተናግሯል። በእጁም ዘጠኝ ኤፍ አንድ ቦንቦች ተይዞውበታል።ተጠርጣሪዎች እንደተናገሩት ከእነርሱ ጋር አብረው 41 ሰዎች ስልጠና ወስደዋል።
በአርባምንጭና የተለያዩ አካባቢዎች የእጅ ቦንቦችን እንዲሁም ከፍተኛ ገንዘብ የያዙ ወጣቶች በቁጥጥር ስር መዋላቻው ይታወቃል። ዶ/ር አብይ የለውጡን እንቅስቃሴ ለመቀልበስ ሙከራዎች ቢኖሩም አይሳካላቸውም በማለት መናገራቸው ይታወሳል።