አርበኞች ግንቦት 7 ማናቸውንም ሰላማዊ ያልሆኑ እንስቃሴዎችን ገታ

(ኢሳት ዲሲ–ሰኔ 15/2010) አርበኞች ግንቦት 7 ማናቸውንም ሰላማዊ ያልሆኑ እንስቃሴዎችን ከዛሬ አርብ ሰኔ 15 /2010 ጀምሮ መግታቱን አስታወቀ።

ይህ ርምጃ በኢሕአዴግ ውስጥ ያሉ ቀልባሽ ሃይሎች ከፍተኛ መስዋዕትነት የተከፈለበትን የለውጥ እንቅስቃሴ ለመቀልበስ የሚያደርጉትን የቀቢጸ ተስፋ ርምጃ ለማምከን ያለመ መሆኑንም አስታውቋል።

“በሃገራችን የዲሞክራሲ ለውጥ ለማምጣት ተገደን የገባንበትን ማንኛውንም ሰላማዊ ያልሆነ እንቅስቃሴ ገተናል” በሚል ርዕስ አርበኞች ግንቦት 7 ባወጣው ልዩ መግለጫ ከሁለት ቀናት በፊት ከለውጥ ሃይሉ ጋር መሰለፉን ግልጽ ማድረጉን አስታውሷል።

ይህንንም ሲያብራራ “መግለጫችን ደጋግሞ ለማስረዳት እንደሞከረው አርበኞች ግንቦት 7 ከማናቸውም አመጾች ነፃ የሆነ ሰላማዊና የሰለጠነ የፖለቲካ ትግል ወደ እውነተኛ ዲሞክራሲ ሊወስደን የሚችል አስተማማኝ የትግል ስልት መሆኑን አስገንዝቧል። በሃገራችን የአመጽ ትግል አስፈላጊነት የመነጨው ራስን ከአሸባሪው የወያኔ አገዛዝ ለመከላከል ሲባል ብቻ የተወሰደ አማራጭ ያልነበረው መፍትሄ በመሆኑ ነበር ።” ሲልም ተገዶ የጀመረውን የዓመጽ መንገድ ለመመርመር የሚያስችል ሁኔታ በኢትዮጵያ መፈጠሩን ገልጿል።

መግለጫውን ሲቀጥልም   “ኢህአዴግ ውስጥ የተነሳውና በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ የሚመራው የለውጥ ሃይል እየወሰደ ባለው እጅግ አበረታች እንቅስቃሴ የሃገራችንን ፖለቲካ ከአመጽ ነጻ በሆነ ሰላማዊ እና ስልጡን ፖለቲካ ከግብ ማድረስ እንደሚቻል ተስፋ ስለፈነጠቀ፤ እየታየ ያለውን አበረታች እንቅስቃሴ ለማገዝ ሰኔ 8 እና 9 ልዩ ስብሰባውን ያካሄደው የንቅናቄያችን ሥራ አስፈጻሚ ወቅታዊውን ሁኔታ ከገመገመ ቦኋላ የሚከተለውን ውሳኔ አስተላልፏል።” በማለት ውሳኔውን አስታውቋል ።

“ከዛሬ ሰኔ 15 ቀን 2010 ዓም ጀምሮ አርበኞች ግንቦት 7 በማናቸውም መልኩ በየትኛውም የሃገሪቱ  ክፍሎች ምንም አይነት አመጽ ነክ እንቅስቃሴ ከማድረግ ታቅቧል።

በዚህ ውሳኔ መሠረት ኢትዮጵያ ዉስጥ በየትኛዉም አካባቢ የሚገኙ የነጻነት ታጋዮቻችን ከማናቸውም የአመጽ እንቅስቃሴ እንዲታቀቡ ድርጅታዊ ትዕዛዝ ተላልፎላቸዋል።

ይህ ርምጃ በኢህአዴግ ውስጥ ያሉ ቀልባሽ ሃይሎች የኢትዮጵያ ህዝብ ከፍተኛ መስዋዕትነት የከፈለበትን የለውጥ እንቅስቃሴ ለመቀልበስ የሚያደርጉትን የቀቢፀ ተስፋ ርምጃዎች ለማምከን የሚያስፈልገውን ማንኛውንም ጥንቃቄ ግምት ውስጥ ያስገባና ፤ የተጀመረው የለውጥ እንቅስቃሴ ሰላማዊ ገጽታውን ይዞ እንዲሄድ ለማበረታታት የታለመ በራስ ተነሳሽነት የተወሰደ ውሳኔ ነው።”  ሲልም መግለጫውን ቋጭቷል።