ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ በሚካሄደው ሰልፉ ላይ ይገኛሉ ተባለ

(ኢሳት ዲሲ–ሰኔ 15/2010)ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ ነገ በአዲስ አበባ ከተማ በሚካሄደው ሰልፍ ላይ ይገኛሉ ተባለ።

የሰልፉ አስተባባሪዎች በጠየቁት መሰረት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ቅዳሜ ሰኔ 16/2010 በሚካሄደው ትዕይንተ ሕዝብ ላይ እንደሚገኙ የመንግስት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት አስታወቋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለም ለነገው ሰልፍ የሚደረገው ዝግጅት ቀጥሏል።

ፌደራል ፖሊስ ሰልፉ በሰላም እንዲጠናቀቅ ዝግጅት ማድረጉንም አስታውቋል።

በሚሊየኖች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ይታደሙበታል በተባለው የነገው የመስቀል አደባባይ ትዕይንተ ሕዝብ ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደሚገኙ መገለጹ የተሳታፊውን ቁጥር ይበልጥ ከፍ እንደሚያደርገው ተገምቷል።

ከአዲስ አበባ ባሻገር ከአጎራባች የኦሮሚያ ክልል ከተሞች በርካታ ፈረሰኞችም እንደሚሳተፉ የተገለጸ ሲሆን በውጭ በሚኖሩ ኢትዮጵያውያንም ዘንድ እየተጠበቀ ይገኛል።

የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድን የለውጥ ጉዞ በመደገፍና በርሳቸውና በቡዳናቸው ላይ ትንኮሳ የሚያደርጉ ሃይሎችን ለመቃወምና ለማሳሰብ በአዲስ አበባ መስቀል አደባባይ የተጠራው ይህ ሰልፍ ዝግጅት ቀጥሏል።

በደሴና በጎንደር ከተሞችም ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድን በመደገፍ ለነገ ሰልፍ መጠራቱ ታውቋል።

ነገ በአዲስ አበባ መስቀል አደባባይ የሚካሄደው ሰልፍ ያለምንም የጸጥታ ችግር እንዲከናወን የፌደራል ፖሊስ ዝግጅት ማድረጉ ተገልጿል።

የፌደራል ፖሊስ እንዳስታወቀው የጸጥታ ችግር እንዳይኖር ከተደረገው ዝግጅት ባሻገር ወደ መስቀል አደባባይ የሚያስገቡ መንገዶች ዳር መኪና ማቆም የተከለከለ መሆኑንም አስታውቋል።

በሰልፉ የሚታደሙ ኢትዮጵያውያን የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ፎቶግራፍ  ያለበትን ካናቴራ በስፋት እየገዙ መሆናቸው በምስል ተደግፈው ከተሰራጩት መረጃዎች መመልከት ተችሏል።

በተመሳሳይ ቀን በጎንደርና በደሴ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይን ለመደገፍ የተጠራ ሰልፍ የሚካሄድም መሆኑ ታውቋል።

በኦሮሚያ ክልል ከተሞችም ሰልፉ እንደሚቀጥል ታውቋል።

በደቡብ ክልል የቦንጋ ከተማ ነዋሪዎች ለጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ድጋፍ የጠሩት ሰልፍ መከልከሉን ለማወቅ ተችሏል።