(ኢሳት ዲሲ–ሰኔ 13/2010) በአዲስ አበባ ለመጭው ቅዳሜ የተጠራው ሕዝባዊ ሰልፍ በከተማው አስተዳደር ጽሕፈት ቤት እውቅና እንደተሰጠው ታወቀ።
ጽሕፈት ቤቱ ሕገመንግስቱ ከሚደነግገው አሰራር ውጭ በእውቅና መስጫ ደብዳቤው ለሰልፉ ፈቃድ ሰጥቻለሁ ማለቱም ተገልጿል።
“ለውጥን እንደግፍ ዲሞክራሲን እናበረታታ”በሚል መርህ በተጠራው ሰልፍ በአዲስአበባ በሚሊየኖች የሚቆጠር ሕዝብ ይገኛል ተብሎም ይጠበቃል።
የአዲስ አበባ አስተዳደር ሰልፉ መንግስትን ለመደገፍ የተጠራ ነው ማለቱን አስተባባሪዎቹ ትክክል አይደለም ሲሉ ተቃውሟቸውን አሰምቷል።
በመጪው ቅዳሜ በአዲስ አበባ የሚካሄደው ግዙፍ ሰልፍ በኢትዮጵያ እየታየ ያለውን ለውጥ ለመደገፍና ይህንን ሂደት የሚያደናቅፉትን ለማውገዝ ነው።
በመስቀል አደባባይ ላይ የሚካሄደውን ሰልፍ ለማከናወንም በርካታ መፈክሮች መዘጋጀታቸውንና ልዩ ልዩ ካኒቴራዎች መታተማቸውን አስተባባሪዎቹ ገልጸዋል።
መፈክሮቹና ካኒቴራዎቹ የያዟቸው መፈክሮችም በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ የተጀመሩ የለውጥ ሔደቶችን የሚደግፉ መሆናቸው ነው የተገለጸው።
የድጋፍ ሰልፉ መሪ ቃል “ለውጥን እንደግፍ ዲሞክራሲን እናበረታታ” የሚል ቢሆንም የአዲስ አበባ አስተዳደር ግን በከተማዋ መስቀል አደባባይ የሚካሄደው ሕዝባዊ ስብሰባ መንግስትን ለመደገፍ የተጠራ በመሆኑ ፈቃድ ሰጥቻለሁ ብሏል።
በኢትዮጵያ ሕገ መንግስት ማንኛውንም ሰልፍ ለማካሄድ ከ24 ሰአት በፊት ማሳወቅን ከመጠበቁ ውጪ ፈቃድ መጠየቅን አይገልጽም።
እናም ቢሮው በሕጉ መሰረት እውቅና ሰጥቻለሁ ማለት ቢጠበቅበትም ፈቃድ ሰጥቻለሁ ማለቱ ሕጉን የሚጻረር መሆኑን የሕግ ባለሙያዎች ይናገራሉ።
በሚሊየን የሚቆጠረው የአዲስአበባና የአካባቢዋ ሕዝብ በነቂስ ወጥቶ በመስቀል አደባባይ በመጪው ቅዳሜ እንደሚታደም ይጠበቃል።
በዚሁ ግዙፍ ሰልፍም የለውጥ ሂደቱን የሚያደናቅፉ የገዥው ፓርቲ የቀድሞ አመራሮች ይወገዛሉ ተብሏል።
በሰልፍ ላይ የተጀመረው ዲሞክራሲያዊ ለውጥ ቀጥሎ በሃገሪቱ የሽግግር መንግስት እንዲኖርና በርካታ አፋኝ ሕጎች ይሻሩ የሚሉ ጥያቄዎችም ይቀርባሉ ተብሎ ይጠበቃል።