(ኢሳት ዲሲ–ሰኔ 7/2010) የሕወሃት ማዕከላዊ ኮሚቴ ባካሄደው አስቸኳይ ስብሰባ በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አስተዳደር ላይ ቅሬታውን አቀረበ።
የኢሕአዴግ ስራ አስፈጻሚ ባድመን በተመለከተ ያሳለፈውን ውሳኔ እንዲሁም ግዙፍ የመንግስት ተቋማት በከፊል ወደ ግል እንዲዞሩ የተደረሰበትን ስምምነት ግን እንደሚቀበለው አረጋግጧል።
የእስከዛሬው ድላችንም ሆነ የነገው ስኬታችን በአብዮታዊ ዲሞክራሲያዊ መስመር ብቻ ነው ብሏል የሕወሃት ማዕከላዊ ኮሚቴ።
ይህ ተግባራዊ መስመር በኢሕአዴግ አመራር እየተሸረሸረ ነው ሲልም ማዕከላዊ ኮሚቴው ቅሬታውን አቅርቧል።
እየተካሄደ ያለውን የስልጣን ድልድል በተመለከተም ከኢሕአዴግ ሕገ ደንብ ያፈነገጠ ነው ያለው ሕዝባዊ ወያኔ ሃርነት ትግራይ ለድርጅታችን ነባር አመራሮች እውቅና እንዲሰጥና አስቸኳይ ጉባኤ እንደጠራ ሲልም ጥሪ አቅርቧል።
የሕወሃትና ማዕከላዊ ኮሚቴ ነባሮቹን አመራሮች አቶ ስብሃት ነጋን፣አቶ ስዩም መስፍንና አቶ ዘርአይ አስገዶምን ጨምሮ ከሰኔ 3 እስከ 5 በመቀሌ ያካሄደውን አስቸኳይ ስብሰባ ተከትሎ ያወጣው መግለጫ በፓርቲውና በስርአቱ ውስጥ ያለውን ጥርጣሬና ቅሬታ በግልጽ አንጸባርቋል።
የ43 አመታት የድልና የጽናት ጉዟችን ስኬት ምንጭ የጠራና ብቁ አብዮታዊ መስመር የዘለቅን መሆኑ ነው ያለው የሕወሃት ማዕከላዊ ኮሚቴ ያለፉት 27 አመታት የስልጣን አመታት ድልና የወደፊቱም ስኬት በአብዮታዊ ዲሞክራሲ የጠራ መስመር እንደሆነ አመልክቷል።
ሆኖም ይህንን ሃገራችንን ከጥፋት የታደገ የብሔር ብሔረሰቦችን እኩልነት ያረጋገጠና ተአምርን የፈጠረ መስመር በአሁኑ ሰአት በኢሕአዴግ አመራር እየተሸረሸረ በከፋ የጥገኝነት ዝቅጠት አረንቋ ውስጥ ገብቷል ሲል ሕወሃት ገልጿል።
ይህንን ፈተና ለማለፍ በድርጅታችን የተጀመረው በጥልቀት የመታደስ እንቅስቃሴ በሚፈለገው ደረጃ ሊሳካ አልቻለም ሲልም ሕወሃት አስታውቋል።
የኢሕአዴግ ስራ አስፈጻሚ የኢትዮ-ኤርትራ የድንበር ኮሚሽን ውሳኔን ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ለመቀበል ያሳለፈውን ውሳኔ እንዲሁም ግዙፍ የሀገሪቱን ተቋማት በከፊል ለመሸጥ የደረሰበት ድምዳሜ ተገቢና ከመስመራችን ጋር የተጣጣመ ነው ያለው ሕወሃት ሆኖም ከሕዝብ ጋር ሳይመክር በአደባባይ መገለጽ አልነበረበትም ሲል ቅሬታውን አቅርቧል።
የኢሕአዴግ ስራ አስፈጻሚ ለሃገሪቱ ኢኮኖሚ ችግር ዘላቂ መፍትሄ ላይ መወያየት ሲገባው ችግሩ ባስከተላቸው ውጤቶችና ጊዜያዊ መፍትሄዎች ላይ ማተኮሩ ግን ተገቢ አይደለም ሲል ሕወሃት የኢሕአዴግን አመራር ተችቷል።
በኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ሳቢያ ከኑሯቸውና ከስራቸው ተፈናቅለው ሉአላዊነት በማስከበር ለቆዩት የአካባቢው ሚሊሺያና ሕዝብ ከፌደራል መንግስት ጭምር በቂ ድጋፍ እንዲያገኙ መወሰኑንም አስታውቋል።
በዲሞክራሲና በጥገኝነት መካከል ትግል እየተካሄደ ይገኛል ያለው የሕወሃት ማዕከላዊ ኮሚቴ የኢሕአዴግን ሕገ ደንብና ተቋማዊ አሰራር ያልተከተለ የአመራር ምደባ እየተካሄደ ነው በማለት የሹመት አሰጣጡ እርምት እንዲደረግበት ጠይቋል።
ለረጅም ጊዜያት በሕወሃት ውስጥ ተይዘው የነበሩት የብሔራዊ መረጃና ደህንነት እንዲሁም ኢንሳና ሜቴክን ጨምሮ በርካታ የሃላፊነት ቦታዎች ላይ በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አስተዳደር አዳዲስ ሰዎች መመደባቸው ይታወቃል።
ሕወሃት ለድርጅታችን ነባር አመራሮች እውቅና ይሰጥ ሲልም ጥሪ አቅርቧል።
የማንነትና የወሰን ጥያቄዎች በሚገባ መልስ የተሰጣቸው በመሆናቸው የትግራይን ሕዝብ አንድነትና ሰላም ለመረበሽ የሚደረጉ እንቅስቃሴዎችን ከትግራይ ሕዝብ ጋር በመሆን በጽናት እንታገላለን ሲልም አስታውቋል።
የትግራይ ሕዝብና ሕወሃት የአብዮታዊ ዲሞክራሲ መስመር ደጀን በመሆን ትግላቸውን እንደሚያጠናክሩም አስታዉቋል።
በሕጋዊና ሰላማዊ መንገድ ከሚንቀሳቀሱ ሃይሎች ጋር አብረን ለመስራት ዝግጁ ነን ያለው ሕወሃት ከጸረ-ሕወሃትና ከጸረ-ትግራይ የውስጥና የውጭ ሃይሎች ጋር አምርሮ ትግሉን እንደሚቀጥል አስታውቋል።
ወቅታዊውን ሁኔታ በፍጥነት ለመገምገም የኢሕአዴግ ስራ አስፈጻሚ አስቸኳይ ስብሰባ እንዲጠራም ሕወሃት ጥሪ አቅርቧል።