የአለም ዋንጫ በሩሲያ ሞስኮ ተጀመረ

(ኢሳት ዲሲ–ሰኔ 7/2010) 21ኛው የአለም ዋንጫ ዛሬ በሩሲያ ሞስኮ ከተማ ተጀመረ።

በአለም ዙሪያ በቢሊየን የሚቆጠሩ ተመልካቾችን በመሳብ ግንባር ቀደም ሆኖ የተገኘው የአለም የእግር ኳስ ዋንጫ ከአፍሪካ የሚሳተፉ 5 ቡድኖችን ጨምሮ 32 ሀገራት ተሳታፊ ሆነውበታል።

ከዛሬ ሰኔ 7/2010 ጀምሮ እስከ ሐምሌ 8/2010 የሚቆየው የአለም ዋንጫ በሩሲያ ሞስኮና ፒትስበርግን ጨምሮ በ11 ከተሞች የሚካሄድ ነው።

ሩሲያም ይህንን እድል ስታገኝ የመጀመሪያዋ ነው ተብሏል።

በዚህ በ21ኛው የአለም ዋንጫ ከአፍሪካ የሚሳተፉት ሃገራት ግብጽ፣ናይጄሪያ፣ሴኔጋል፣ሞሮኮና ታንዛኒያ ናቸው።

አፍሪካ ለረጅም አመታት በሁለት ከለቦች ብቻ ተገድባ መቆየቷ ይታወሳል።

የአፍሪካ ተወዳዳሪዎች ቁጥር እንዲጨምር የአፍሪካን ፉትቦል ፌዴሬሽን ለ16 አመታት የመሩት ኢትዮጵያዊው አቶ ይድነቃቸው ተሰማ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማድረጋቸው ሲዘገብ ቆይቷል።