(ኢሳት ዲሲ–ሰኔ 6/2010)ኢሕአዴግ የአልጀርሱን ስምምነት ያለምንም ቅድመ ሁኔታ መቀበሉን በመቃወም የኢትዮጵያ ድንበር ጉዳይ ኮሚቴ ለጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ደብዳቤ ላከ።
መቀመጫውን በአሜሪካ ያደረገው ኮሚቴው በላከው ደብዳቤ ላይ እንደገለጸው በበቂ ማስረጃ ባልተደገፈ መልኩ የተደረገው ስምምነት የኢትዮጵያን ጥቅም የሚጎዳ በመሆኑ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በኢህአዴግ በኩል የተወሰነውን ውሳኔ እንዲያጤኑት ጠይቋል።
የኢትዮጵያ ድንበር ጉዳይ ኮሚቴ የኢትዮጵያን መሬት ለሱዳን አሳልፎ በመስጠት በህወሃት በኩል እየተደረገ ያለውን ሴራ እንዲያስቆሙትም በደብዳቤው ጥሪ ማድረጉን ለማወቅ ተችሏል።
የኢትዮጵያ ድንበር ጉዳይ ኮሚቴ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ የላከው ደብዳቤ ሲጀምር በዶክተር አብይ በጎ ተግባራት የተሰማውን ደስታ በመግለጽ ነው።
ኮሚቴው በጠቅላይ ሚኒስትሩ እየተደረጉ ያሉ ጅምር እንቅስቃሴዎች ተስፋ የሚሰጡ በመሆናቸው አድናቆት የሚቸራቸው እንደሆነ ገልጿል።
በመቀጠል በኢህአዴግ በኩል የተወሰደውንና የአልጀርሱን ስምምነት የተመለከተውን ውሳኔ እንዲሁም ለሱዳን ተላልፈው የተሰጡና ሊሰጡ በዝግጅት ላይ ስላሉ መሬቶች ጉዳይ ያሳስበኛል በማለት ስጋቱን በዝርዝር ያስቀመጠበት መሆኑን ለኢሳት ከደረሰው መረጃ ለማወቅ ተችሏል።
የኢትዮጵያ ድንበር ጉዳይ ኮሚቴ እንዳለው የኢሕአዴግ መንግሥት ሥልጣን ከመያዙ በፊት፤ ኢትዮጵያን ያስተዳድሩ የነበሩት መንግሥታት፤ በአስተዳደር ብልሹነት ይወቀሱና ይጠየቁ እንደሆነ እንጂ፤ የሃገራቸውን ሉዓላዊነትና የግዛት አንድነት በማስከበር የኢትዮጵያን ህልውና በማስጠበቅ ረገድ ታግለው ያታገሉ መሆናቸውን የታሪክ ገድላቸው ሕያው ምስክር ነው።
ይሁን እንጂ ኢሕአዴግ ሥልጣን ከያዘበት ጊዜ ጀምሮ የአገራችንን የግዛት አንድነት የተዳፈሩና የኢትዮጵያን ካርታ የቀየሩ ርምጃዎች የኢትዮጵያ ሕዝብ ባልመከረበት ሁኔታ ለሌላ አገር አሳልፎ ተሰቷል።
ኢትዮጵያ የባሕር በሯን እና ሰሜናዊ ክፍሏን አስረክባ ዛሬ የባዕድ አገር ወደብ ተጠቃሚ ከሆነች 27 ዓመታት ተቆጥረዋል ሲል የኢትዮጵያ ድንበር ጉዳይ ኮሚቴ በደብዳቤው ጠቅሷል።
እስከዛሬ ድረስ የኢትዮጵያ ሉዓላዊነትና የግዛት አንድነት ባተኮሩ የድንበር ስምምነቶች የኢትዮጵያ ሕዝብ ሳያውቀውና ሳይመክርበት፣ የአገራችን ጥቅምና የፀጥታ ጉዳይ ሳይገመገም፣ የታሪክና የባለቤትነት ሰነዶች በአግባቡ በመረጃነት ሳይቀርቡ የሚደረጉ በመሆናቸው ስንቃወም ቆይተናል።
ዛሬም ገና ከጅምሩ በኢትዮጵያ ጥቅም ላይ ባልተመሰረተና በተሳሳተ የቅኝ ግዛት ሰነድ መነሻነት በተወሰነው የአልጀርስ የድንበር ስምምነት ውሳኔ መሠረት ያደረገ የድንበር መሬት የማስረከብ ሂደትን በከፍተኛ ደረጃ እንቃወማለን በማለት የድንበር ጉዳይ ኮሚቴው አቋሙን ገልጿል።
በመሆኑም ይህ ከፍተኛ ሕዝባዊ ተቃውሞ ያስነሳው የአልጀርስ የድንበር ስምምነት ውሳኔ አፈጻጸም፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ በግልጽ በሚያውቀውና በሚወስንበት ሁኔታ እንዲሆን አጥብቀን እንጠይቃለን ሲል የኢትዮጵያ ድንበር ጉዳይ ኮሚቴ ለጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ በላከው ደብዳቤ ላይ አመልክቷል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከአጎራባች ሃገራት ጋር በጋራ ተባብሮ ለመኖር የሚያደርጉትን ከፍተኛ ጥረት እያደነቅን፤ ኢትዮጵያ ከአጎራባች አገራት ጋር በሰላም ለመኖር የራስዋን ጥቅም አሳልፋ መስጠት አይጠበቅባትም ብለን እናምናለን በማለትም የኢትዮጵያ መሬቶች ለሱዳን ተላልፈው የመሰጠታቸውን ሴራ በመጥቀስ መልዕክቱን አስተላልፏል።