ኦህዴድ ከ2ሺ የሚበልጡ አባላቱን አባረረ

(ኢሳት ዲሲ–ሰኔ 6/2010) የኦሮሞ ሕዝብ ዲሞክራሲያዊ ድርጅት/ኦህዴድ/ባካሄደው 8ኛ ጉባኤው ከ2ሺ የሚበልጡ አባላቱን አባረረ።

ከ500 የሚበልጡ የድርጅቱ አባላትን ደግሞ ከደረጃቸው ዝቅ እንዲሉ ማድረጉ ተሰምቷል።

ለድርጅቱ ቅርበት ያላቸው ወገኖች እንደገለጹት ኦሕዴድ ምንጠራ ያካሄደባቸው እነዚህ ግለሰቦች ነዋሪዎችን በአስተዳደር የበደሉ የሌላ አካባቢ ተወላጆች ናቸው ያሏቸውን ሰዎች ደሞ ከቀያቸው ያባረሩና ያቆሳቆሉ ናቸው።

ትላንት ማክሰኞ የሶስት ቀናት ድርጅታዊ ጉባኤውን ያጠናቀቀው የኦሮሞ ሕዝብ ዲሞክራሲያዊ ድርጅት/ኦሕዴድ/ በክልሉና በአጎራባች ክልሎች መካከል ያለውን የድንበር ግጭት እንዲሁም በክልሉ በሚኖሩ የሌላ አካባቢ ተወላጆች በሚል የሚፈናቀሉ ነዋሪዎችን በተመለከተ መነጋገሩ ታውቋል።

ሕገወጥ የመሬት ወረራን ጨምሮ በክልሉ ይካሄዳሉ ያላቸውን ሕገ ወጥ ድርጊቶችና የውሸት ሪፖርቶችን ጭምር የገመገመው የኦሮሞ ሕዝብ ዲሞክራሲያዊ ድርጅት/ኦሕዴድ/ በዚህ ሒደት ተሳታፊ ናቸው የተባሉ ከ2000 የሚበልጡ የዞን፣ የወረዳና የቀበሌ አመራሮችን አባሯል።

540 የሚሆኑትንም ከደረጃ ዝቅ አድርጓል።

ከአባልነት ያባረራቸው በርካቶች መሆናቸው ተመልክቷል።

በዶክተር አብይ አህመድና በአቶ ለማ መገርሳ የሚመራው የኦሮሞ ሕዝብ ዲሞክራሲያዊ ድርጅት/ኦሕዴድ/በከፍተኛው አመራር ላይ የታየው ዲሞክራሲያዊነትና የሕግ የበላይነት ግንዛቤ ወደ ዝቅተኛውና መካከለኛው እርከን በተገቢው መንገድ አለመስረጹ በክልሉ ለሚፈጠሩ ችግሮች ምክንያት እንደሆነም ተጠቅሷል።

የራሳቸውን ጥቅም የሚያሳድዱ ወገኖች ደግሞ ችግሩን እያባባሱ መገኘታቸው ተመልክቷል።

ከቅርብ ግዚያት ወዲህ የኦሮሚያ ክልል ከጌዲዮ ተወላጆች ጋር ከፍተኛ ደም አፋሳሽ ግጭት መደረጉ ይታወሳል።

በብዙ ሺዎች የሚቆጠሩ የጌዲዮ ተወላጆችም ተፈናቅለዋል።

ከተለያዩ የኦሮሚያ አካባቢዎች የአማራ ተወላጆችም የተፈናቀሉ ሲሆን ወደ እስር ቤት የገቡ መኖራቸውም ታውቋል።

ከሶማሌ ክልል ጋርም ያለው ግጭት ለወራት መፍትሔ ሳያገኝ ቀጥሏል።

ከነዚህ ግጭቶች በስተጀርባ በሀገሪቱ እየተካሄደ ያለውን ሒደት ያለተቀበሉ ወገኖች ከኦሕዴድ አንዳንድ የቀድሞ መሪዎችና በድርጅቱ ውስጥ ከቀረው ኔትወርክ ጋር በትብብር የሚፈጽሙት እንደሆነ አንዳንድ የኦሕዴድ ምንጮች ይገልጻሉ።

አሁን ኦሕዴድ ያካሄደው ምንጠራ ችግሩን ይቀንሰዋል የሚል ተስፋ ተጥሎበታል።