(ኢሳት ዲሲ–ሰኔ 5/2010) የሲዳማ ብሄረሰብ የዘመን መለወጫ በዓል መከበር መጀመሩ ተገለጸ።
ፍቼ ጨምበላላ በሚል መጠሪያ የሚከበረው በዓል በብሄረሰቡ ዘንድ ትልቅ ስፍራ ያለው ባህላዊ ፌስቲቫል ነው።
ከሀዋሳ ዙሪያ በሺዎች የሚቆጠሩ የብሄረሰቡ ተወላጆችና የአከባቢው ነዋሪዎች በባህላዊ አልባሳት ደምቀው እያከበሩት መሆኑንም የደረሰን ዜና ያመለክታል።
ፍቼ ጨምበላላ የማይዳሰሱ ቅርሶች በሚል በመንግስታቱ ድርጅት የባህልና የሳይንስ ተቋም ዩኒስኮ ከተመዘገቡ የሀገራችን በዓላት አንዱ እንደሆነም ይታወቃል።
የሲዳማ ሴት ከጋብቻ በኋላ በዓመት አንድ ጊዜ ወደ ቤተሰቦቿ የምታደርገውን ጉዞ በማስታወስ የሚከበር በዓል ነው ፍቼ ጨምበላላ። ይህቺ ሴት ወደ ቤተሰቦቿ ስታመራ በቆጮና በቅቤ የሚሰራ ቡርሳሜ የተሰኘ ባህላዊ ምግብ አዘጋጅታ መሆኑን መረጃዎች ያመለክታሉ። ቡርሳሜውን ቤተሰቦቿ ከጎረቤቶቻቸው ጋር በመሆን እየተመገቡ ጊዜውን በደስታ የሚያሳልፉበት ልዩ ወቅት ነው። ይህ ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲሸጋገር የቆየው ታሪክ የሲዳማ ህዝብ በዓመት አንድ ጊዜ የሚውለውን የፍቼ ጨምበላላ በዓል መነሻ ተደርጎ ተመዝግቧል። ፍቼ ጨምበላላ የሲዳማን ህዝብ አንድነትና ፍቅር የሚያንጸባርቅ መድረክ ሆኖ ለዘመናት ሲከበር የቆየ በዓል ነው።
በየዓመቱ የብሄረሰቡ አዋቂዎች መክረው ኮከብ ቆጥረው የበዓሉን ዕለት የሚወስኑ እንደነም ለማወቅ ተችሏል። አዋቂዎች ፍቺ ጨምበላላ የሚውልበትን ቀን ከወሰኑ በኋላ ለሀገር ሽማግሌዎች ያሳውቃሉ። ለበዓሉ የሚደረግ ዝግጅት ቀኑ ከታወቀበት ጊዜ አንስቶ ይጀመራል። ለአንድ ሳምንት ያህል የሚቆየውና በጭፈራና ዳንስ የሚከበረው ፍቼ ጨምበላላ በብሄረሰቡ አባላትና በአከባቢው ነዋሪዎች ዘንድ ልዩ ስፍራ የተሰጠው በዓል ነው። የዕድሜና የጾታ ልዩነት ሳይገድብው ሁሉም የህበረተሰብ ክፍል በእኩል ስሜት የሚያከብሩት በዓል እንደሆነም ይነገራል። በዓሉ በሚከበርበት ሳምንት የመጀመሪያው ቀን ልጆች ቤት ለቤት በመሄድ ለጎረቤቶቻቸው መልካም ምኞትና ሰላምታ በማቅረብ የበዓሉ ጊዜ ይጀምራል። ጎረቤትም ለበዕሉ የተዘጋጀውን ቡርሳሜ የተሰኘ ባህላዊ ምግብ በማቅረብ ልጆቹን ያስተናግዷቸዋል። በበዓሉ ላይ የሀገር ሽማግሌዎችና የብሄረሰቡ መሪዎች ለህዝቡ ምክርና የመልካም ምኞት መልዕክት ያስተላልፋሉ። ጠንክሮ ስለመስራት ስለመከባበር፡ በዕድሜ የገፉትን ስለመርዳት፡ በሀገር ሽማግሌዎቹ ከሚተላለፉት መልዕክቶች የሚጠቀሱ ናቸው። የተጣሉ የሚታረቁበት የዕርቅ በዓልም እየተባለ የሚጠቀስ ነው ፍቼ ጨምበላላ። ወላጆች ለልጆቻቸው የበዓሉን ትክክለኛ ትርጉም በማስተማር ሳይበረዝና ሳይከለስ ከትውልድ ትውልድ እንዲተላለፍ እንደሚያደርጉም ይነገራል።
ፍቼ ጨምበላላ በማይዳሰዱ ቅርሶች በሚል በመንግስታቱ ድርጅት የሳይንስና የባህል ተቋም ዩኔስኮ ከተመዘገቡ የሀገራችን ክብረበዓላት አንዱ መሆኑም ታውቋል። በዓሉ በዋዜማው ዛሬ በተለይ በሀዋሳ ከተማ ዋና ዋና መንገዶች ላይ በጭፈራና ዳንስ እየተከበረ መሆኑንም ለማወቅ ተችሏል። በተያያዘ ዜና የፍቼ ጨምበላላ በዓል በሚከበርባት በሀዋሳ ከተማ ብሄርን መነሻ ያደረገ ጥቃት መፈጸሙን የኢሳት የመረጃ ምንጮች ገልጸዋል። ዛሬ በሀዋሳ ከተማ ገበያ ብሄር ላይ ያተኮረ ጥቃት የተፈጸመ ሲሆን በሰውና በንብረት ላይ ጉዳት መድረሱን ለማወቅ ተችሏል። ኢሳት ያነጋገራቸው የሲዳማ ሀርነት ንቅናቄ አመራር አባል አቶ ለገሰ ላንቃሞ ፍቼ ጨምበላላ የሰላምና የፍቅር በዓል ነው፡ ይህን መልካም ገጽታ ለማበላሸት የሚንቀሳቀሱ ሃይሎችን አጥብቀን እናወግዛለን ብለዋል።