(ኢሳት ዲሲ–ሰኔ 5/2010)የሶማሌ ክልል ልዩ ፖሊስ ባሳለፍነው ሳምንት 14 ሰዎች መግደሉን ተከትሎ አምንስቲ ኢንተርናሽናል መግለጫ አወጣ።
ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተከራክረው አምንስቲ ኢንተርናሽናል የሶማሌ ልዩ ፖሊስ ካልታገደ በሰዎች ላይ የሚደርሰው ግፍና ሰቆቃ ማቋረጫ የለውም ብሏል።
የሶማሌ ልዩ ፖሊስ በጭናቅሰን ወረዳ በፈጸመው ጥቃት በርካታ ሰዎች መገደላቸውን አምንስቲ ኢንተርናሽናል አረጋግጧል።
ሽብርተኝነትን ለመከላከል በሚል በሶማሌ ክልል የተቋቋመው ልዩ ፖሊስ እርሱ ራሱ ሰዎችን አሸባሪ ከሆነ ሰነባብቷል። የሶማሌ ልዩ ፖሊስ ከተቋቋመ ወዲህ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች መገደላቸው ነው የሚነገረው። በተለይ ደግሞ ከኦሮሚያ ክልል ጋር በተፈጠረ የአዋሳኝ ድንበር ግጭት ከ1 ሚሊየን በላይ ሰዎች ሲሰደዱ ብዙዎቹም ተገድለዋል፤ የአካል ጉዳትም ደርሶባቸዋል።
ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት የከራካሪ ዓምንስቲ ኢንተርናሽናል ታድያ የሶማሌ ክልል ልዩ ፖሊስ ካልታገደ በስተቀር ግድያው ሊቆም እንደማይችል ሲያስጠነቅቅ ነበር። እንዳለውም አልቀረ በሰሞኑ ብቻ በጭናቅሰን ወረዳ የተለያዩ አካባቢዎች በሶማሌ ልዩ ሃይል በተፈጸመ ጥቃት 14 ሰዎች ተገድለዋል ነው ያለው። ቆቦ ቢካ፣ ኡላን ኡላ እና ዋሌንሱ በተባሉት ሶስት አካባቢዎች ብቻ 3 ሰዎች ሲገደሉ ሌሎች 3 ሰዎች ደግሞ ቆስለዋል ተብሏል። ዳርቢጋ እና ጎሎቻ በተባሉ ሌሎች ሁለት አካባቢዎችም 7 ሰዎች ተገድለው ተጨማሪ 17 ሰዎችም እንደቆሰሉም ነው የተነገረው።
እናም አምንስቲ ኢንተርናሽናል ደጋግሞ እንደገለጸው የሶማሌ ልዩ ሃይል በመንግስት እንደፈረሰ ካልተደረገ ሰቆቃውና ግፍ ይቀጥላል ሲል አስጠንቅቋል።
የአምንስቲ ኢንተርናሽናል የምስራቅ አፍሪካ እና የታላላቅ ሃይቆች ዳይሬክተር ጁምን ኒያንዮኪ እንዳሉት በሶማሌ ልዩ ፖሊስ በሚፈጸመው ጥቃት የሰው ሕይወት መጥፋቱ ካልቆመ ችግሩ አሳሳቢ መሆኑ ይቀጥላል። ስለሆነም መፍትሄው የሶማሌ ልዩ ሃይልን ማገዱና ለማፍረስ ብቻ ነው ሲሉም ዳይሬክተሩ ተናግረዋል።