(ኢሳት ዲሲ–ሰኔ 1/2010) ታዋቂው የሲ ኤን ኤን የምግብ ዝግጅት ተራኪና ጋዜጠኛ አንቶኒ ቦርዲያን ከዚህ አለም በሞት ተለየ።
አንቶኒ ቦርዲያን በፈረንሳይ ሆቴሉ ውስጥ ራሱን ገድሎ መገኘቱን የአለም መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።
የ61 አመቱ አንቶኒ ቦርዲያን በመላው አለም በመዞር ምግብ ነክ ዘጋቢ ፊልሞችን በማዘጋጀት ታዋቂነትን ከማትረፉም በተጨማሪ አለም አቀፍ ሽልማቶችንም አግኝቷል።
አንቶኒ ቦርዲያን ዛሬ ጠዋት ለስራ ጉዳይ ባቀናባት ፈረንሳይ ሆቴል ውስጥ ራሱን ገድሎ መገኘቱን ሲ ኤን ኤን በዘገባው አረጋግጧል።
ሲ ኤን ኤን ባወጣው መግለጫ እንዳለው የአንቶኒ ቦርዲያን ሞት እጅግ የሚያሳዝንና የሚያስደነግጥ ነው።
አንቶኒ ቦርዲያን በስራዎቹ በአለም ዙሪያ የሕዝብን የአመጋገብ ባህል ያስተዋወቀና የተለየ ተሰጥኦ ያለው ተራኪ ነበርም ተብሏል።
በዚህ አስቸጋሪ ወቅትም ለአንዲት ሴት ልጁና ቤተሰቦቹ መጽናናትን በመመኘት ነፍሱ እንድትማር እንጸልያለን ሲልም ሲ ኤን ኤን የተሰማውን ጥልቅ ሀዘን ገልጿል።
“ያልታወቀው ስፍራ” የተሰኘው ተከታታይ ተራኪ ፊልምን የሚያዘጋጀው አንቶኒ ቦርዲያን በዚህ ፕሮግራሙ የተነሳ አለም አቀፍ ሽልማት ማግኘቱ ይታወቃል።
በአንቶኒ ቦርዲያን ያልታሰበ ሞት ምክንያት ታዋቂ ጋዜጠኞችና አርቲስቶች እንዲሁም በመላው አለም የሚገኙ ተመልካቾቹና አድናቂዎቹ ከፍተኛ ድንጋጤ እንደተሰማቸው የአለም መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።
በምግብ ዝግጅት የስራ ሕይወቱን የጀመረው አንቶኒ ቦርዲያን በኋላም ጸሀፊና ጋዜጠኛ በመሆን በሲ ኤን ኤን ቴሌቪዥን ታዋቂነትን ያተረፈ የፕሮግራም አዘጋጅ እስከመሆን ደርሷል።
አንቶኒ ቦርዲያን በተለያዩ የአለም ዙሪያዎች የምግብ አይነቶችን በመቅመስ ለሌላው ሲያዩት የማያምር የሚመስለውን እጅግ ጣፋጭ ምግብ በርካቶች እንዲወዱት ማድረግም ችሏል።
ታዋቂው የሲ ኤን ኤን ጋዜጠኛ አንቶኒ ቦርዲያን በኢትዮጵያ በነበረው ቆይታም ማርቆስ ከተባለው ትውልደ ኢትዮጵያዊ ምግብ አዘጋጅ ጋር እጅግ መሳጭ ፕሮግራም መስራቱም ይታወሳል።
ይህ በእንዲህ እንዳለም በአሜሪካ ኒዮርክ ነዋሪ የነበረችው ታዋቂ ዲዛይነር ኬት ስጌይድ በተመሳሳይ ሁኔታ እራሷን ማጥፋቷ ይታወሳል።
ዲዛይነሯ አጠቃላይ ሃብቷ ከ3 ቢሊየን ዶላር በላይ መሆኑንም ዘገባዎች አመልክተዋል።