በአማሮ ወረዳ ያለው ግጭት ዛሬ ቀጥሎ መዋሉ ተሰማ

በአማሮ ወረዳ ያለው ግጭት ዛሬ ቀጥሎ መዋሉ ተሰማ
(ኢሳት ዜና ሰኔ 1 ቀን 2010 ዓ/ም) ካለፈው ሃምሌ ወር ጀምሮ በአማሮ ወረዳ በጉጂ እና በኮሬ ማህበረሰብ መካከል የተጀመረው ግጭት ዛሬም ቀጥሎ በመዋሉ የዜጎች ህይወት አልፏል። ከኮሬ በኩል በዳኖ ቡልቶ ቀበሌ የ49 ዓመቱ አርሶ አደር ሰንበተ ሳንኩራ እና የ42 ዓመቱ ጎልማሳ ቶማስ ገመደ ከብቶቻቸዉን በማገድ ላይ እንደነበሩ ሲገደሉ፣ ከ30 በላይ የቤት እንስሶቻቸው ተዘርፎባቸዋል። ይህን ተከትሎም ከፍተኛ የተኩስ ልዉዉጥ እየተደረገ ነው። ከአማሮ ወደ ዲላ የሚወስደው መንገድ ተዘግቶ መዋሉንም የደረሰን መረጃ ያመለክታል።
እስካሁን ባለው መረጃ በአለፈው አንድ አመት ውስጥ በኮሬ በኩል ብቻ 52 ሰዎች ሲገደሉ፣ ከ100 በላይ የሚሆኑ ሰዎች ደግሞ ቆስለዋል። በጉጂ ኦሮሞዎች በኩል የሞቱትን ቁጥር ማወቅ አልተቻለም።
የጉጂ ማህበረሰብ ከቡርጂ፣ ከኮሬና ከጌድዮ ማህበራሰቦች ጋር ተደጋጋሚ ግጭቶችን ማድረጉን መዘገባችን ይታወቃል። አብዛኞቹ ግጭቶች የተነሱት ከድንበር ማካለል ጋር ተያይዞ ነው።በአካባቢው የተሰማሩት ወታደሮች ግጭቶችን ለማስቆም አለመቻላቸው የአካቢውን ሀዝብ እያስቆጣ ይገኛል።