(ኢሳት ዲሲ–ሰኔ 1/2010) በትግራይ ክልል የኢሮብ ወረዳ ሕዝብ የአልጀርሱ ስምምነት ተግባራዊ እንዳይሆን በመጠየቅ ሰላማዊ ሰልፍ አደረጉ።
የኢሮብ ነዋሪዎች የአልጀርሱ ስምምነት ከሁለት የሚከፍለን በመሆኑ እንቃወማለን ብለዋል።
ሕወሃት በበኩሉ የአልጀርሱን ስምምነት በሚመለከት ባወጣው መግለጫ የኢሕአዴግ ጽሕፈት ቤት የኢትዮ-ኤርትራ የድንበር ኮሚሽንን ውሳኔ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ መቀበሉ ተገቢ ነው ብሏል።
በጉዳዩ ላይም የትግራይ ክልል ርዕሰ መስተዳድርና የሕወሃት ሊቀመንበር ዶክተር ደብረጺዮን ገብረሚካኤል መግለጫ እንደሚሰጡ ተነግሯል።
በትግራይ ክልል የኢሮብ ወረዳ ነዋሪዎች የአልጀርሱ ስምምነት ተግባራዊ እንዳይደረግ በሰላማዊ ሰልፍ ተቃውሟቸውን ገልጸዋል።
ምክንያታቸው ደግሞ ስምምነቱ ተግባራዊ ቢደረግ የኢሮብ ወረዳ ለሁለት ተከፍሎ ሕዝቡም ይለያያል በሚል ነው።
በመሆኑም የኢሕአዴግ መንግስት ጥያቄያችንን አዳምጦ መፍትሄ ይስጠን ሲሉ መጠየቃቸውን የወረዳው የኮሚኒኬሽን ጽሕፈት ቤት ሃላፊ ወይዘሮ ሰላም ሃጎስ ገልጸዋል።
የኢሮብ ሕዝብ በትግራይ ክልል ከሚገኙ ብሔረሰቦች አንዱ ነው።
የአልጀርሱ ስምምነት ተግባራዊ ከተደረገ ሕዝቡ ከሁለት ስለሚከፈል ምናልባትም ነዋሪዎቹን ወደ ትግራይ ማስፈር ግድ እንዲሆን ሊያደርግ ይችላል ተብሏል።
ይህ በእንዲህ እንዳለም የሕዝባዊ ወያኔ ሃርነት ትግራይ ስራ አስፈጻሚ ኢሕአዴግ የአልጀርሱን ስምምነት መቀበሉ ተገቢ ነው ብሏል።
ሕወሃት በጉዳዩ ላይ ምክክር ሲያደርግ ቆይቶ ውሳኔ ላይ በመድረሱ የቀረበ ጥሪ መሆኑንም የስራ አስፈጻሚው መግለጫ ያመለክታል።
እንደ ሕወሃት መግለጫ ከሆነ የትግራይ ሕዝብ በኢትዮጵያና ኤርትራ መካከል ሰላም እንዲሰፍን በተደጋጋሚ ጠይቋል።
እናም የአልጀርሱ ውሳኔ ተግባራዊ መሆኑ ለሰላም ይበጃል ነው ያለው የሕወሃት መግለጫ።
የአልጀርሱን ስምምነት ተግባራዊ ለማድረግ ግን ቀጣይ ውይይት እንደሚያስፈልግ ሕወሃት ገልጿል።
በተያያዘ ዜና የአልጀርሱ ስምምነት ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ተግባራዊ እንዲደረግ ኢሕአዴግ መወሰኑን በተመለከተ የሕወሃቱ ሊቀመንበር ዶክተር ደብረጺዮን ገብረሚካኤል መግለጫ ይሰጣሉ ተብሎ ይጠበቃል።