ሜቴክ የሃገሪቱን ሃብት በከፍተኛ ደረጃ እያበከነ ነው ተባለ

(ኢሳት ዲሲ–ሰኔ 1/2010)  የብረታብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን /ሜቴክ /የሃገሪቱን ሃብት በከፍተኛ ደረጃ  በማባከን ላይ መሆኑ በፓርላማው ተገለጸ።

ኮርፖሬሽኑ ውስጥ ባለው ችግር ሰራተኞች  ከሥራ እየለቀቁ መሆናቸውም ተመልክቷል።

የስኳር እና የማዳበሪያ ፕሮጀክቶችን በተመለከተ እየቀረበ ያለውም ሪፖርት የተምታታና የማይታመን መሆኑም  በፓርላማው ተገልጿል።

መንግስታዊው የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ረቡዕ ባወጣው ዘገባ በሕወሃት የጦር ጄኔራሎች ሲመራ የቆየው ሜቴክ በዘጠኝ ወራት ውስጥ  ያባከነው የሃገሪቱ ሃብት ከ9 ቢሊዮን ብር በላይ ነው።

በፓርላማው የመንግስት ልማት ድርጅቶች ቋሚ ኮሚቴ የኮርፖሬሽኑን የ9 ወራት አፈጻጸም በገመገመበት ወቅት ተቋሙ የገበያ ጥናት ሳያደርግ ከ9 ቢሊዮን ብር በላይ  የሚገመቱ የተለያዩ ማሽኖች ፣መለዋወጫ እቃዎችና መሳሪያዎችን በማምረት አከማችቶ ማስቀመጡ ተገልጿል።

የሃገሪቱን ኢኮኖሚ ሊያግዝ በሚችል መልኩ በጥናት ላይ ተመስርቶ እንደማይሰራም የኮሚቴው አባላት ገልጸዋል።

የብረታብረት ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን ሜቴክ በየጊዜው ለምክር ቤቱ የሚያቀርባቸው ሪፖርቶች ወጥነት የጎደላቸውና የሚዋዥቁ መሆናቸውንም የምክር ቤቱ አባላት ገልጸዋል።

በዚህ ረገድ የያዩ  ማዳበሪያ  እንዲሁም የኦሞ ኩራዝ አንድ እና የበለስ ቁጥር አንድ ስኳር ፋብሪካዎች ግንባታ አፈጻጸምን በተመለከተ አምና የቀረበው ሪፖርት ከዘንድሮው ጋር የተጋጨ መሆኑን የፓርላማው ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ መተቸታቸውም ተመልክቷል።

አምና ግንባታቸው ከ 90 በመቶ በላይ ተጠናቀቁ የተባሉ ፕሮጀክቶች ዘንድሮ ደግሞ  ዝቅ ብለው ሪፖርት መደረጋቸውን ገልጸዋል።

በቅርቡ የሜቴክን  ዋና ዳሬክተርነት ከሕወሃቱ  ጄነራል ክንፈ ዳኘው የተረከቡት  ዶክተር  በቀለ ቡላዶ ፕሮጀክቶች በተያዘላቸው ጊዜ እየተከናወኑ አይደሉም፤የውጤታማነትና የሃብት ብክነት እንዳለባቸው አረጋግጠናል ብለዋል ፤

ለወደፊቱ ችግሮቹን ለማስተካከል እንደሚሰሩ ለፓርላማ አባላት ቃል መግባታቸውንም ኢዜአ ዘግቧል።

ኮርፖሬሽኑ ባለበት የአስተዳደር ችግርና አነስተኛ ክፍያ ሳቢያ ሠራተኞች ኮርፖሬሽኑን በመልቀቅ ላይ መሆናቸውም በፓርላማው ተገልጿል።