ታህሳስ 19 ቀን 2004 ዓ/ም
ኢሳት ዜና:- በስፍራው የሚገኘው የኢሳት ወኪል ያደረሰን መረጃ እንደሚያመለክተው፤ በካምፓላ- በደህንነቶች የመታፈን አደጋ ተጋርጦባቸው በከፍተኛ ውጥረት ውስጥ ከሚገኙት አምስት ሰዎች መካከል፤ በቅርቡ የፈጠራ የሽብርተኝነት ክስ የተመሰረተበት የመኢዴፓ ሊቀመንበሩ አቶ ዘለለ ፀጋሥላሴ እና ጋዜጠኛ ደረጀ በጋሻው ግንባር ቀደሞቹ ናቸው።
በቅርቡ እዚያው ካምፓላ ውስጥ የነበረ ሩዋንዳዊ የፖለቲካ ስደተኛ በታጠቁ ሀይሎች መገደሉን ያስታወሰው የኢሳት ዘጋቢ፤ በኡጋንዳ የሚገኘው የተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ጉዳይ ጽህፈት ቤት የፖለቲካ ስደተኞችን በመለየት ተገቢውን “ፕሮቴክሽን” በመስጠት በኩል የሚያሳየው ቸልተኝነት በስደተኞቹ ላይ እየደረሰ ላለው አደጋ እንደ ዋነኛ ምክንያት የሚጠቀስ ነው ብሏል።
በመሆኑም ጉዳዩ የሚመለከታቸው የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾችና በውጪ አገር የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን በአደጋ ውስጥ የሚገኙትን ኢትዮጵያውያን ድምፅ ለዓለማቀፉ ህብረተሰብ በማሰማትና ካምፓላ ለሚገኘው የተመድ የስደተኞች ጉዳይ ጽህፈት ቤት ስልክ በመደወልና ደብዳቤ በመፃፍ ግፊት ያደርጉላቸው ዘንድ ተማጽነዋል።
በቅርቡ የፈጠራ የ ሽብርተኝነት ክስ ከተመሰረተባቸው መካከል አቶ አቤል አለማየሁ በካርቱም እየኖረ ሳለ በሱዳን መንግስት አማካይነት ለወያነ ተላልፎ መሰጠቱ ይታወሳል።