27 የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) አመራርና አባላት ታሰሩ

19 ቀን 2004 /

ኢሳት ዜና:-በደቡብ ኢትዮጵያ  በጎፋ ልዩ ዞን በዘንጋ አዋንዴ ቀበሌ ውስጥ 27 የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) አመራርና አባላት በገዢው ፓርቲ ታጣቂዎች መታሰራቸውን መኢአድ አስታወቀ፡፡

የደምባ ጎፋ ወረዳ ምክር ቤት ሰብሳቢ አቶ ማዩ ማይጠሎ በበኩላቸው፣ የተጠቀሱት የመኢአድ አባላት የታሰሩት በአካባቢው እየተከናወነ ያለውን የልማት ሥራ ለማደናቀፍ በመንቀሳቀሳቸው ነው ይላሉ።
መኢአድ  እንዳስታወቀው፣ ታኅሣሥ 16 ቀን 2004 ዓ.ም. ከታሰሩት የመኢአድ አባላት መካከል፤ ስድስቱ የፓርቲው አመራሮች ናቸው፡፡
በጎፋ ልዩ ዞን የዘንጋ አዋንዴ ቀበሌ የመኢአድ ሰብሳቢ አቶ ኢልካዩ ኤሮ፣ ምክትል ሰብሳቢው መምህር አየለ ታደሰ፣ ዋና ጸሐፊው አቶ ዘሪሁን እኩሌ፣ የመኢአድ ሥራ አስፈጻሚ አባል የሆኑት አቶ ኢሳያስ ዘርቦ፣ ሃምሳ አለቃ ማናዬ ሞላልኝና አቶ መንግሥቱ ማናዬ- ታኅሣሥ 16 ቀን 2004 ዓ.ም. ከቀኑ 10፡00 ሰዓት አካባቢ በመኢአድ ጽሕፈት ቤት ውስጥ በስብሰባ ላይ እያሉ በፖሊሶች ታፍነው መታሰራቸውን ድርጅቱ አስታውቋል።

ሌሎቹ ሃያ አንድ የዘንጋ አዋንዴ ቀበሌ የመኢአድ ሥራ አስፈጻሚዎችና አባላት የታሰሩትም ከላይ በተጠቀሰው ቀን ምሽት የወረዳው የኢሕአዴግ ባለሥልጣናት የመኢአድ አባላት በሚኖሩበት አካባቢ አሰሳ እንዲካሄድ ካዘዙ በኋላ መሆኑንም  መኢአድ ገልጿል፡፡

የዳምባ ጎፋ ወረዳ የምክር ቤት ሰብሳቢ አቶ ማዩ ማይጠሎ ፣ የመኢአድ አባላት የታሰሩት የክልሉ መንግሥት በአካባቢው እያከናወነ ያለውን የተፋሰስ ልማት ለማደናቀፍ ሲንቀሳቀሱ በመገኘታቸው ነው ብለዋል፡፡

እርሳቸው እንዳሉት፣ በደምባ ጎፋ ወረዳ የተፋሰስ ሥራ ለመሥራት ለቀያሾች ሥልጠና እየተሰጠና ጐን ለጐን ሌሎች የልማት ሥራዎች እየተከናወኑ ባሉበት በአሁኑ ጊዜ፣ ሃያ ሰባቱ የመኢአድ አባላት ‹‹የተፋሰስ ሥራውን አንሠራም›› ብለው በመቃወማቸው በፖሊስ ቁጥጥር ሥር ሊውሉ ችለዋል፡፡

ይሁንና ፦”ሥራ አልሠራም” ብሎ  ተቃውሞን በዝምታ መግለጽ እንዴት ልማትን ማደናቀፍ ሊሆን እንደሚችል ፤የወረዳው ምክር ቤት ሰብሳቢ ያስረዱት ነገር የለም።

የመኢአድ ሥራ አስፈጻሚ አባልና የደቡብ ኢትዮጵያ ቀጣና ኃላፊ አቶ እንድሪያስ ኤሮ በበኩላቸው ፣ የመኢአድ አባላት የታሰሩት ልማት በማደናቀፋቸው ሳይሆን ፤የግለሰቦችን ማሳ አንቆፍርም ብለው በመቃወማቸው እንደሆነ ተናግረዋል።

በአካባቢው የሚገኘውን የግለሰቦች ማሳ ከመቆፈር ይልቅ ነዋሪዎች በጋራ የሚጠቀሙበትን መሬት ለተፋሰስ ሥራ ማዋል የተሻለ እንደሚሆን በመጠቆም ለቀበሌው ኃላፊዎች በጽሑፍ ጥያቄ ማቅረባቸውን የገለጹት አቶ እንድሪያስ፣ ይህ የመቃወም መብት ልማት እንደማደናቀፍ ተወስዶ የመኢአድ አባላት ለእስር መዳረጋቸውን አስታውቀዋል፡፡

‹‹የዜጎች የመናገርና የመጻፍ መብት የተጠበቀ ነው፡፡ ተቃዋሚዎች ማንኛውንም ነገር የመቃወም መብት አላቸው፤›› የሚሉት አቶ እንድሪያስ፣ የደምባ ጎፋ ወረዳ ባለሥልጣናት ግን ሕገ መንግሥቱ ለዜጐች የሰጠውን መብት በመጣስ ሰላማዊ ዜጐችን እያሰሩ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

‹‹ዜጎች በመንግሥት ባለሥልጣናት የሚወሰኑ ውሳኔዎችን መቃወም አይችሉም ወይ?›› የሚል ጥያቄ በሪፖርተር የቀረበላቸው የወረዳው ምክር ቤት ሰብሳቢ አቶ ማዩ ማይጠሎ ግን፣ ‹‹ይህ የልማትና የሕይወት ጉዳይ ነው፡፡ እነሱ ካልሠሩ ማን መጥቶ ሊሠራላቸው ነው? አንሠራም ማለት አይችሉም፤›› የሚል ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

አክለውም የወረዳው መስተዳድር፦ በመኢአድ አባላት ላይ ‹‹ልማትን በማደናቀፍ››  ክስ ለመመሥረት እየተንቀሳቀሰ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

መኢአድ እንዳለው፣በአሁኑ ጊዜ ሁሉም የመኢአድ አመራርና አባላት ከሚኖሩበት አካባቢ 17 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ከሚገኘው የሻውላ ከተማ ታስረዋል፡፡