የአህባሽን እምነት ለመከተል ፈቃደኛ አልሆኑም የተባሉ 10 የእስልምና እምነት ተከታዮች ታሰሩ

ታህሳስ 19 ቀን 2004 ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-በሰሜን ጎንደር በአድርቃይ ወረዳ ነዋሪ የሆኑት ሙስሊሞች የታሰሩት ፣ የአህባሽን አስተምህሮ የሚያስፋፉት የሙስሊም አባላት ላቀረቡት ጥያቄ መልስ ለመስጠት ፈቃደኛ አልሆኑም ተብሎ ነው።

ያለምንም ጠያቂና የፍርድ ቤት ሂደት ካለፈው አንድ ወር ጀምሮ ሙስሊሞቹ እየተሰቃዩ መሆኑን የደረሰን መረጃ ያመለክታል።

እስረኞቹ “የድረሱልን ጥሪ” ማሰማታቸውን አንድ ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ የሙስሊሞቹ የአካባቢው ተወካይ ለኢሳት ተናግረዋል።

“ፍርድ አጣን፣ በአገራችን መኖር በማንችልበት ደረጃ ደርሰናል” የሚሉት ተወካዩ፣ መንግስት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ሙስሊሙን ማእከል ያደረገ የጥቃት ዘመቻ በግልጽ መክፈቱንም ተናግረዋል።

በደቡብ ጎንደር ዞን በወረታ ከተማ ነዋሪ የነበሩት አቶ   የሱፍ ሙሀመድ  ጥቅምት ስድስት ቀን ከምሽቱ አንድ ሰአት ላይ ላይ በመጥረቢያ ተመትተው መሞታቸውን ቤተሰቦቻቸውን በማናገር መዘገባችን ይታወሳል።

ግለሰቡ አል ሱናን በመተው ወደ አህባሽ እንዲቀላቀሉ ከአህባሽ እምነት ተከታዮች ተደጋጋሚ ማስጠንቀቂያ ሲሰጣቸው ቆይቷል።

የፌደራል ጉዳዮች ሚኒስትር የሆኑት ዶ/ር ሽፈራው ተክለማርያም፣ መጤውን የዋህቢ እምነት ከአገሪቱ ጠራርጎ ለማስወጣት እና አገር በቀል የሆነውን እምነት እንዲከተል ሙስሊሙ በጋራ እንዲነሳ በአለማያ ተገኝተው ንግግር ማድረጋቸው ይታወሳል።