(ኢሳት ዲሲ–ግንቦት 15/2010)የነጻነት ታጋዩ አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ በሚቀጥለው ሳምንት እንደሚፈታ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ ገለጹ።
ዶክተር አብይ አሕመድ ትላንት በብሔራዊ ቤተመንግስት ከትግራይ ተወላጆች ጋር ባካሄዱት ውይይት እንዳሉት ኢትዮጵያ አንዳርጋቸው ጽጌን በማሰሯ በቢሊየን የሚቆጠር ዶላር አጥታለች።
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ የተበላሸውን ኢሕአዴግ የማስተካከል ርምጃ እየወሰድኩ ነው ብለዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ በብሔራዊ ቤተመንግስት በተካሄደው ስነስርአት ላይ እንደተናገሩት አቶ አንዳርጋቸው ጽጌን ኢሕአዴግ ማሰሩ ተገቢ ሆኖ አልተገኘም።
እንዲያውም የአቶ አንዳርጋቸው መታሰር ኢትዮጵያን ጎድቷታል ነው ያሉት።
ዶክተር አብይ እንደገለጹት ኢትዮጵያ አቶ አንዳርጋቸው ጽጌን በማሰሯ ከእንግሊዝ መንግስት ልታገኝ የምትችለውን በቢሊየን የሚቆጠር ዶላር አሳጥቷታል፡፡
እናም አቶ አንዳርጋቸውን ማሰር ጥቅም ስለሌለው ከሌሎች ባለሃብቶች ጋር በሚቀጥለው ሳምንት ይፈታል ብለዋል።
ከአቶ አንዳርጋቸው ጽጌ መፈታት ጉዳይ ጋር በተያያዘም ከከፍተኛ ባለስልጣናት ጋር ብዙ ንትርክና ክርክር እንደነበርም አልሸሸጉም።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ በብሔራዊ ቤተመንግስት ለትግራይ ተወላጆች በተካሄደው የእራት ግብዣ ላይ ሌሎችንም ጉዳዮች አንስተዋል።
የቪዲዮ ቀረጻም ሆነ ሞባይል እንዳይገባ በተከለከለበት በዚሁ ስነስርአት በጡረታ የተገለሉ የኢሕአዴግ ባለስልጣናት አብዛኞቹ እንዳኮረፉም ነው የተናገሩት።
እንደ አቶ አብይ ገለጻ ከአቶ ታደሰ ሃይሌ በስተቀር በጡረታ የተገለሉት ባለስልጣናት በተወሰነው ውሳኔ አኩርፈዋል።ይህም ተገቢ አይደለም ነው ያሉት ።
ዶክተር አብይ አህመድ በሊቢያ የታረዱና በግብጽ የተቀበሩ ኢትዮጵያውያን አስከሬንን ለማምጣት በሚቀጥለው ሳምንት ወደ ካይሮ እንደሚያመሩም ተናግረዋል።
የኢትዮጵያውያኑ አስከሬን በሃገራቸው በክብር እንዲያርፍ እንደሚደረግም በመግለጽ ።
ከኤርትራው ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ጋር ለመነጋገር በሳውዲው ንጉስ በኩል ሞክረውም እንዳልተሳካላቸው ዶክተር አብይ ተናግረዋል።
በኢትዮጵያ ዘረኝነት ባስከተለው ችግር አንድ የትግሬ ባለስልጣን ሹፌሩንም ጸሃፊውንም ዘበኛውንም ከራሱ ብሔር ያደርግ እንደነበር ዶር አብይ መናገራቸውን በግብዣው ላይ የተገኙ ምንጮች ገልጸዋል።
ይህ ማለት ግን በትግራይ ሕዝብ ስም የሚንግዱ የሚያደርጉት እንጂ አብዛኞቹ በድህነት ውስጥ የሚኖሩ ናቸው ብለዋል።