የዋልያ ቢራ ሰራተኞች የስራ ማቆም አድማ አደረጉ
(ኢሳት ዜና ግንቦት 13 ቀን 2010 ዓ/ም) በሆላንዱ ታዋቂ የቢራ ፋብሪካ ሃይነከን የተገነባው ቂሊንጦ በሚገኘው የቢራ ፋብሪካ ውስጥ በመጫንና በማውረድ ስራ ላይ የተሰማሩ ከ500 የማያንሱ ሰራተኞች መብታችን አልተከበረልንም በሚል የስራ ማቆም አድማ አድርገዋል። አድማው ካለፈው ቅዳሜ ጀምሮ በመካሄድ ላይ ሲሆን፣ በፋብሪካው የተመረቱ የቢራ ምርቶች ሳይሰራጩ ቀርተዋል።
ሰራተኞቹን በኮንትራት የሚያሰራቸው ኤዶምያስ ኢንተርናሽናል ሃላፊነቱ የተወሰነ የግሉ ኩባንያ የተባለው ድርጅት የተለያዩ የሰብአዊ መብቶችን እንደሚጥስ የሚናገሩት ሰራተኞች፣ ዋናው ፋብሪካ ሰራተኞችን በቀጥታ ቀጥሮ እንዲያሰራቸው ጠይቀዋል።
የሃይንከን ባለስልጣናት ችግሩን አይተው መፍትሄ እንደሚሰጡዋቸው ቃል እንደገቡላቸው ሰራተኞች ተናግረዋል። የተመረቱ ምርቶችም ሆኑ ከሽያጭ የተመለሱ የቢራ ሳጥኖች ሳይወርዱ መቅረታቸውን ሰራተኞች ተናግረዋል።