በአርቢትር ኢያሱ ፈንቴ ላይ ድብደባ በመፈጸማቸው ቅጣጥ ከተጣለባቸው የወልዋሎ ተጫዋቾእች መካከል የአምስቱ ቅጣት እንዲነሳ ተደረገ።

በአርቢትር ኢያሱ ፈንቴ ላይ ድብደባ በመፈጸማቸው ቅጣጥ ከተጣለባቸው የወልዋሎ ተጫዋቾእች መካከል የአምስቱ ቅጣት እንዲነሳ ተደረገ።
(ኢሳት ዜና ግንቦት 14 ቀን 2010 ዓ/ም) ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ-ከመከላከያ ጋር ባደረገው ጨዋታ ላይ የመሀል ዳኛ ኢያሱ ፈንቴ የሰጡትን ውሳኔ በመቃወም የወልዋሎ ተጫዋቾችና የቡድን መሪው ዳኛውን መሀል አስገብተው የፈጸሙት ድብደባ ብዙዎችን ማሳዘኑና ማነጋገሩ ይታወሳል።
ድርጊቱን ተከትሎ “ዳኞች ዋስትና ካልተሰጠን ዳግም አናጫውትም”፡በማለታቸው ፕሪሚየር ሊጉ ለተወሰነ ጊዜ ተቋርጦ የነበረ ሲሆን፣ የእግርኳስ ፌዴሬሽንም በወልዋሎ ቡድን መሪና በተጫዋቾቹ ላይ ቅጣት መጣሉ ይታወቃል።
ይሑንና፣ አርቢትር ኢያሱ ፈንቴ “ከተፈጸመብኝ ድብደባ ይልቅ ዘር እየጠቀሱ የሰነዘሩብኝ ስድብ ነው ይበልጥ ያመመኝ” በማለት የነበረውን እውነታ በአደባባይ በማጋለጣቸው፣ የህወኃት ሹመኞችና ደጋፊዎች በዳኛ ኢያሱ ፋንቴ ላይ ቁጣና ተቃውሞ ሲገልጹ ሰንብተዋል።
እነዚሁ የህወኃት ሰዎች፦“ክስተቱት ያልሆነ መልክ በማስያዝ ለፖለቲካ ፍጆታቸው እየተጠቀሙበት ነው” በማለት ነው አርቢትር ኢያሱን የከሠሱዋቸው።
ዳኛ ኢያሱ ፋንቴ የነበረውን እውነታ ከመግለጽ ውጭ ከራሳቸው ፈጥረው የተናገሩት ነገር እንደሌለ፣ እንዲሁም ለሕዝብ አብሮ መኖር ሲባል የተሰነዘሩባቸውን አሳፋሪ ስድቦች ሁሉ ከመግለጽ እንደተቆጠቡ በመናገር ነው ለከሳሾቻቸው ምላሽ የሰጡት።
የህወኃት ሰዎች በአርቢትሩ ላይ የያዙትን ጠንካራ ተቃውሞ ተከትሎም በቅርቡ በወልድያ ጥቃት ለተፈጸመባቸው ሌላ ዳኛ የመቶ ሺህ ብር ካሳ ሢሰጥ፣ መሬት ላይ ተጥለው በበርካታ ተጫዋቾችና በቡድን መሪው ለተደበደቡት ለዳኛ ኢያሱ ፋንቴ የገንዘብም ሆነ የሞራል ካሳ አልተሰጣቸውም።
ከዚህም ባሻገር የፌዴሬሽኑ ውሳኔ ሳይውል ሳያድር በዛሬው ዕለት በአምስት የወልዋሎ ተጫዋቾች ላይ የተላለፈው የቅጣት ውሳኔ ሙሉ በሙሉ እንዲነሳ ተደርጓል።
የነበረው ሁኔታ በመንግስት መገናኛ ብዙሀን ሳይቀር ይፋ በሆነበት ሁኔታ “ተጨዋቾቹ ከበባ ከማድረግ ውጭ ዳኛውን አልመቷቸውም”በማለት ነው ቅጣቱ እንዲሻር የተደረገው።
ኢያሱ ፋንቴ ካሳ ያላገኙትም ሆነ-በተጫዋቾቹ ላይ የተጣለውን ቅጣት እንዲነሳ የተደረገው፣ አርቢትሩ በዘራቸው እንደተሰደቡ ማጋለጣቸው ገዥዎቹን ስላመማቸው ነው የሚሉት ታዛቢዎች፣ ይህ የእግድ ማንሳት ብይን-ፍትህንና ህግን ያልተከተለ ፖለቲካዊ ውሳኔ እንደሆነ ግልጽ ነው ይላሉ።
ስለ ጉዳዩ የተጠየቁት አርቢትር ኢያሱ ፈንቴ ፦ኢትዮጵያ ውስጥ ፍትህ የለም ፡ወደ ይግባኝ ኮሚቴም ቅሬታ አላቀርብም፡፡ጉዳዩን ወደ አለም አቀፍ እግር ኳስ አስተዳዳሪ ወይም ፊፋ እወስደዋለሁ”ብለዋል።