የሐረሪ ክልል ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ ገቢሳ ተስፋዬ ከስልጣን ተነሱ
(ኢሳት ዜና ግንቦት 10 ቀን 2010 ዓ/ም) በሃረሪ ክልል የሚኖሩ የኦሮሞ ተወላጆችን ጥያቄዎች በአግባቡ አልመለሱም ሃላፊነታቸውንም በአግባቡ አልተወጡም በሚል ሲተቹ የቆዩት አቶ ገቢሳ ተስፋዬ ከስልጣናቸው ተነስተው ወደ ጨፌ ኦሮምያ ተዛውረዋል።
በእርሳቸው ቦታ አቶ በቀለ ተመስገን የሐረሪ ክልል ኦህዴድ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባልና የክልሉ ሲቪል ሰርቪስ ቢሮ ሃላፊ ተመድበዋል።
በሃረሪ ክልል የሚኖሩ የኦሮሞና የሌሎች ብሄር ተወላጆች በክልሉ ባለስልጣናት ተደጋጋሚ ጭቆናቸው ሲደርሱባቸው ቢቆዩም ፣ ለችግሩ መፍትሄ የሚሰጥ አካል አልነበረም። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የኦሮሞ ተወላጆች ለጥያቄያቸው መልስ የማይሰጥ ከሆነ አንዳንድ የኦሮሞ ህዝብ በብዛት የሚገኝባቸውን ወረዳዎች ወደ ኦሮምያ ክልል እንዲገቡ ጥያቄዎችን እሰከማንሳት ደርሰው ነበር። በተለይ የኦህዴድ ተወካዩ ም/ል ፕሬዚዳንቱ ከሃብሊ ባለስልጣናት ጋር በመሆን የኦሮሞን ህዝብ ጥያቄ ያዳፍናሉ በሚል ሲከሰሱ ቆይቷል።
ሃረሪን የህበሊ በፕሬዚዳንትነት ኦህዴድ ደግሞ በም/ል ፕሬዚዳንትነት እንደሚያስተዳድሯት ይታወቃል። አብዛኛዎቹ የፖለቲካና የኢኮኖሚ የስልጣን ቦታዎች በህብሊ ባለስልጣናትና ደጋፊዎቻቸው መያዛቸውን የክልሉ ነዋሪዎች ይናገራሉ።