“ባለስልጣናቱ ወረው ለመብላት የተዘጋጁ ናቸው” ሲሉ በአማራ ክልል የተለያዩ ከተሞች የሚኖሩ ነዋሪዎች ተናገሩ

“ባለስልጣናቱ ወረው ለመብላት የተዘጋጁ ናቸው” ሲሉ በአማራ ክልል የተለያዩ ከተሞች የሚኖሩ ነዋሪዎች ተናገሩ
(ኢሳት ዜና ግንቦት 10 ቀን 2010 ዓ/ም) በተለያዩ ከተሞች በሃላፊነት ቦታ የተቀመጡ የገዥው መንግስት አመራሮች የድሃውን ህብረተሰብ ችግር ከመፍታት ይልቅ ለራሳቸው ጥቅም የቆሙ በመሆናቸው ፣ሰርተው ሃገሪቱን ከመለወጥ ይልቅ የራሳቸውን ጥቅም ማሳደዳቸውን መቀጠላቸው እንዳማረራቸው በአማራ ክልል የተለያዩ ከተሞች የሚኖሩ አስተያየት ሰጪዎች ተናግረዋል፡፡
አሁን በአመራር ላይ ያለው ትውልድ በአመራር ላይ ሲቀመጥ ህዝብን ከማገልገል ይልቅ “በምን ዓይነት መንገድ ገንዘብ ማግኘት” እንደሚችል በማሰብ የሙስና መረብ በመዘርጋት እንደሚጠመዱ አስተያየት ሰጪዎች ይናገራሉ፡፡ የበላይ አመራሮችም በጥቅም በመገናኘት የተበደሉትን በቸልታ በመመልከት ህዝብ ሲገፋ ዝምታን መምረጣቸውን በችግርነት ያነሳሉ፡፡
“የደርግ መንግስት ኢትዮጵያን አንድ አድርጎ በማስተዳደር ወደር የሌለው ነበር” የሚሉት አስተያዬት ሰጪ ለደርግ ውድቀት ምክንያት የሆኑት በበታች አመራሮች የግፍ አሰራር መሆኑን ያስታውሳሉ፡፡ አስተያዬት ሰጪው አክለውም፣ አሁን በተለያዩ የመንግስት መስሪያ ቤቶች በአመራርነት የሚያገለግሉ የድርጅቱ ሰዎች “የተሰጣቸውን ተልዕኮ ለምን አልፈጸማችሁም?”የሚል ጥያቄም ሆነ እርምጃ ባለመወሰዱ ሁሉም አሰራር ‘ልቅነት’ እንደሚታይበት ተናግረዋል።

የበላይ አመራሮች ከበታቾቹ ጋር በሚያደርጉት የጥቅም ግንኙነት በመተሳሰር ፣ሰርቶ ከመብላት ይልቅ ‘ወሮ ለመብላት’ የተሰለፉ በመሆኑ ህብረተሰቡ ከፍተኛ የመከራ ገፈት ቀማሽ በመሆን እንዲሰቃይ አድርገዋል ሲሉ አስተያየታቸውን አክለዋል።
በሌላ በኩል አስተያዬት የሰጡት የአማራ ክልል ነዋሪ እንደሚናገሩት መንግስት የህብረተሰቡን ችግር አላወቀም ፡፡ አመራሮች በተለያዩ መስሪያ ቤቶች በሙስና ስለ መዘፈቃቸው በህዝብ ቢጋለጥም ፣ምንም አይነት እርምጃ ሳይወሰድ በመቅረቱ አመራሮችን መገምገሙ ዋጋ ቢስ እንደሆነ ህዝቡ ድምዳሜ ላይ ደርሷል ይላሉ።
“ማርና ገንዘብ ጣፋጭ ነው” የሚሉት አስተያዬት ሰጪ መንግስት ችግር አለባቸው የተባሉና በህዝብ ዘንድ ችግር እንዳለባቸው የተጠቆሙትን አመራሮች ላይ እርምጃ እንደማይወስድ ይገልጻሉ።
ሁሉም የበላይ አመራር በሙስና የተዘፈቀ በመሆኑ ነገሮችን በማረሳሳት መሸፈኑ የተለመደ ሲሉ ተናግረዋል፡፡