ታህሳስ 17 ቀን 2004 ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-በመከላከያ ሰራዊት ውስጥ የተፈጠረው ውጥረት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግንባሩ መተካካት እና የብሄር ተዋጽኦን ለማመጣጠን በሚል ሰበብ ከፍተኛ የጦር መኮንኖችን ማባረሩን ተከትሎ የመጣ ነው።
የኢሳት የደህንነት ምንጮች እንደዘገቡት ሰሞኑን 6 ጄኔራሎችና ከ120 በላይ የኮሎኔልነት ማእረግ ያላቸው መኮንኖች ተባረዋል።
የተባረሩት ጄኔራሎች ሁለቱ የትግራይ ፣ 3 የአማራ እና አንድ የኦሮሞ ተወላጅ ናቸው።
በደራሲ ተስፋየ ገብረአብ መጽሀፍ በዳንስ ችሎታው የታወቀው የኦሮሞ ተወላጁ ጄኔራል ባጫ ደበሌም ከተባረሩት ጄኔራሎች መካከል አንዱ ሆኗል።
ከተባረሩት ታዋቂ የትግራይ ጄኔራሎች መካከል በአንድ ወቅት ለመለስ ዜናዊ እጅግ ታማኝ የነበረውና በሁዋላም፣ በታማኝነት ጥያቄ የተነሳ፣ ከጄኔራል ሳሞራ የኑስ ጋር ግጭት ውስጥ የገባው ጄኔራል ዮሀንስ ገብረመስቀል ይገኝበታል።
ከ 3 አመት በፊት የመለስ መንግስት ለጄኔራል ሳሞራ የኑስ የሙሉ ጄኔራልነት፣ ለሙሀመድ ፈረንጂ እና ለአበባው ታደሰ ደግሞ የሊዩተናንት ጄኔራል ማእረግ ሰጥቶ ነበር።
በተመሳሳይ አመትም ሜጀር ጄኔራል ሳእረ መኮንን፣ ሜጄር ጀኔራል ታደሰ ወረደ እና ሜጀር ጄኔራል ባጫ ደበሌ የሊውተናንት ጀኔራል ማእረግ አግኝተዋል።
ብርጋዲየር ጀኔራል ገብራት አየለ ደግሞ ሜጄር ጄኔራል ተብለዋል።
ከአራት አመት በፊት ደግሞ አብረሀ ወልደማሪያም፣ ሞላ ሀይለማርያም፣ አደም ሙሀመድ፣ ገብረእግዚአብሄር መብራቱ፣ ብርሀኑ ጁላ እና ስዩም ሀጎስ ደግሞ የብርጋዴር ጄኔራልነት ማእረግ አግኝተዋል።
በአመቱ ደግሞ ኮሎኔል ክንፈ ዳኘው፣ ገብረሚካኤል ብየነ፣ አከለ አሳየ፣ ህንጻ ወልደጊዮርጊስ፣ ተክለ ብርሀን ካህሳይ፣ ጌታቸው ጊዲና፣ ማሾ በየነ እና ወንዶሰን ተካም እንዲሁ የብርጋዴር ጄኔራልነት ማእረግ ተሰጥቶአቸዋል።
በመከላከያ ሰራዊት ውስጥ የተፈጠረው ውጥረት በቅርቡ የማእረግ እድገት ያገኙትን መኮንኖች ማእከል ያደረገ በመሆኑ ነው ሲሉ ምንጮች ገልጠዋል።
ቅነሳው በመተካካት ፖሊሲ ላይ የተመሰረተ ነው ከተባለ ከጄኔራል ሳሞራ የኑስ ጀምሮ ያሉት ነባር ጄኔራሎች መቀነስ ነበረባቸው የሚሉት ምንጮች፣ የብሄርን ተዋጽኦ ለመጠበቅ ከሆነም አብዛኞቹ ተባራሪ ጄኔራሎች የትግራይ ተወላጆች በሆኑ ነበር ይላሉ።
እንደምንጮች ዘገባ አሁን ከተባረሩት የትግራይ ጀኔራሎች እና ኮሎኔሎች መካከል አብዛኞቹ ከጄኔራል ሳሞራ የኑስ ጋር ከፍተኛ ቅራኔ ውስጥ ገብተው የነበሩ ናቸው።
የተባረሩት የአማራ ተወላጅ ጄኔራሎች ደግሞ በመፈንቅለ መንግስት መኩራ ተከሰው እስር ቤት የገቡትን የብርጋዴር ጄኔራል ተፈራ ማሞን ሀሳብ ይደግፋሉ ተብለው ክትትል ሲደርገባቸው ቆይቷል።
በመከላከያ ውስጥ የሚታየው ውጥረት ከፍተኛ ደረጃ በመድረሱ የመከላከያ ሚኒስቴር እና አንዳንድ ወታደራዊ ካምፖች በልዩ ሁኔታ እየተጠበቁ ነው።
የተባረሩት ጄኔራሎች እስካሁን ተቃውሞአቸውን በይፋ ወደ አደባባይ አላወጡም።
ይሁን እንጅ በሰራዊቱ ውስጥ ያለው ውጥረት ባልተጠበቀ ሁኔታ በመጨመሩ፣ ጄኔራል ሳሞራ የኑስ ልዩ የክትትል ሀይል መመደባቸውን ለማወቅ ተችሎአል።
በሰራዊቱ ውስጥ የተፈጠረው ውጥረት እስከ ምን ደረጃ ሊሄድ እንደሚችል በሚቀጥሉት ተከታታይ ቀናት ሊታወቅ እንደሚችል ምንጮች ገልጠዋል።
የመከላከያ ሚኒስትር የሆኑት አቶ ሲራጅ ፈርጌሳ የሰራዊቱን የብሄር ተዋጽኦ ለመጠበቅ መንግስት የማመጣጠን ስራ እየሰራ ነው በማለት ለፓርላማ መናገራቸውን ተከትሎ ብሄርንና ታማኝነትን ማእከል ባደረገ መልኩ ቅነሳ እየተካሄደ መሆኑን መዘገባችን ይታወሳል።