በአቶ መለስ ሽብርተኞች ናቸው ተብለው በቁጥጥር ሥር የዋሉት ሲዊዲናዊያኑ ጋዜጠኞች የ11 ዓመት ጽኑ እሥራት ተፈረደባቸው

17 ቀን 2004 /

ኢሳት ዜና:-በአቶ መለስ መንግሥት ሽብርተኞች ናቸው ተብለው በቁጥጥር ሥር  የዋሉት ሲዊዲናዊያኑ ጋዜጠኞች መርቲን ካርል ሽብየ እና ፎቶ ጋዜጠኛ ጁሃን ከርል ፐርሰን ዛሬ ጠዋት በከፍተኛው ፍርድ ቤት ሦስተኛ ወንጀል ችሎት የ አሥራ አንድ (11) ዓመት ጽኑ እሥራት ተፈረደባቸው፡፡

በፍርድ ውሳኔው የተበሳጩት የሲዊዲን አምባሳደር የፍርድ ሂደቱ በሚነበብበት ጊዜ ችሎቱን ረግጠው አቋርጠው ወጥተዋል፣ ወደ ችሎት አዳራሽ በግድ ሊመልሳቸው የነበረውንም ፖሊስ ገፍተው አልፈው ወጥተዋል፡፡

ዕረቡ ታህሳስ 11 ቀን 2004 ዓ.ም በዋለው ችሎት ሁለቱን ሲዊዲናዊያን ጋዜጠኞች በሁለተኛው ክስ- የኦብነግ የሽብር ዓላማን በመደገፍ የጋዜጠኝነት ሙያቸውን ከለላ በመጠቀም ወንጀል እና በአራተኛው ክስ- የሀገርንና የአለማቀፍ ሕግ በመጣስ የአገሪቱን የግዛት ወይም የፖለቲካ ሉአላዊነት በመጣስና በሕገወጥ መንገድ ወደ ሀገር ውስጥ በመግባት ወንጀሎች ጥፋተኛ ናቸው ብሎ መወሰኑን ፍርድ ቤቱ አውስቷል፡፡

በክሥ ሁለት ከ 10 ዓመት የማያንስ፣ ከ 15 ዓመት ደግሞ የማይበልጥ እሥራት፤ በክሥ አራት ደግሞ በትልቁ ከ 10 ዓመት በማይበልጥ ጊዜ ሊቀጡ የሚችልበት አግባብ እንዳለ የገለጸው ፍርድ ቤቱ ሁለቱም ክሦች ደረጃ ያልወጣላቸው በመሆኑ ፍርድ ቤቱ እንደ ወንጀሉ ሁኔታ ደረጃውን ይሰይማል በማለት አብራርቶ ሲዊዲናዊያን ጋዜጠኞች ሰሩት ያለውን ወንጀል በመካከለኛ ደረጃ መመደቡን አስታውቋል፡፡

የመሐል ዳኛ ሸምሱ ሲርጋጋ በንባብ እንዳቀረቡት የፌዴራል ዐቃቤ- ሕግ በጋዜጠኞቹ ላይ ባቀረበው ሁለተኛው ክሥ ጥፋተኛ በመሆናቸው ከ 11 ዓመት ከ3 ወር እስከ 14 ዓመት ከ3 ወር የሚያስቀጣቸው ሲሆን ፍርድ ቤቱ ዝቅተኛውን 11 ዓመት ከ 3 ወር መወሰኑን ገልጸው፣ በአራተኛው ክሥ ከ 3 ዓመት ከ 3 ወር እስከ 5 ዓመት ከ 3 ወር ፅኑ እሥራት የሚያስቀጣቸው ቢሆንም ፍርድ ቤቱ ዝቅተኛውን 3 ዓመት ከ 3 ወር በመወሰኑ በድምሩ 14 ዓመት ከ 6 ወር  የሚያስቀጣቸው ቢሆንም ፍርድ ቤቱ አንድ የቅጣት ማቅለያ በመቀበሉ ጊዜው ተቀንሶ በ 11 ዓመት ጽኑ እሥራት እንዲቀጡ ተወስኗል፤ ይግባኝ የማለት መብታቸውም የተጠበቀ ነው ፡፡

ዐቃቤ- ሕግ በበኩሉ ጋዜጠኞቹ በቁጥጥር ሥር ሲውሉ በፌዴራል ፖሊስ በኤግዚቢትነት የተያዙት ላፕቶፕ ኮምፒውተር፣ ዲጂታል ካሜራ፣ የቪዲዮ ካሜራ፣ የድምጽ መቅረጫ፣ ሜሞሪ ካርድ፣ ገንዘብብ መላላኪያ ኤሌክትሮኒክስ መሳሪያ፣ የኮምፒውተር ሃርድ ዲስክ እና ሌሎችም ላይ ፍርድ ቤቱ ውሳኔ እንዲያስተላልፍለት የጠየቀ ሲሆን የተከሳሽ ጠበቆችም ተቃውሞ የለንም በማለታቸው የመሐል ዳኛ ሸምሱ ሲርጋጋ ፈጠን ብለው ለመንግሥት ውርስ እንዲሆን ፍርድ ቤቱ ወስኗል ብለዋል፡፡

አንድ ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ የሲዊዲን ኤምባሲ ተወካይ በመጪው ሃሙስ በሚያዘጋጁት ጋዜጣዊ መግለጫ በጋዜጠኞቹ የፍርድ ውሣኔ ላይ የመንግሥታቸውን አቋም እንደሚያሳውቁ ለሀገር ውስጥ ጋዜጠኞች አስታውቀዋል፡፡

የጋዜጠኞቹ ጠበቃ የሆኑት አቶ አበበ ባልቻ ውሳኔው ትክክል ነው ብለው እንደማያምኑ ለቢቢሰ ተናግረዋል።

ሌላው ስዊድናዊው ጠበቃ ደግሞ ውሳኔውን በጭካኔ የተሞላ ሲሉ አጣጥለውታል።

የስዊድን ጠቅላይ ሚኒስትር ፍሬድሪክ ሪንፌልድት ከመነሻው ጀምሮ ጋዜጠኞቹ ስራቸውን ሲሰሩ የተያዙ በመሆናቸው በአስቸኳይ እንዲለቀቁ እንጠይቃለን ብለዋል።

አምነስቲ ኢንተርናሽናል እንዳለው ደግሞ ጋዜጠኞቹ የተያዙት ተገቢ የሆነ ስራቸውን ሲሰሩ ነው።

የስዊድን የጋዜጠኞች ህብረት ፍርዱ የፖለቲካ ፍርድ ነው ብሎታል። የስዊድን መንግስትም ጋዜጠኞቹ እንዲፈቱ ግፊት እንዲያደርጉ አሳስቦአል።

ሪፖርተርስ ዊዝ አውት ቦርደርስ እንደገለጠው “የፍርድ ቤቱ ውሳኔ የኢትዮጵያ መንግስት  ማንም ወደ ኦጋዴን ሄዶ በዚያ አካባቢ የደረሰውን የሰብአዊ መብት ጥሰት እንዳያጋልጥ ለማድረግ ነው።