(ኢሳት ዲሲ–ግንቦት 8/2010)በብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት የአገር ውስጥ ደኅንነት ኃላፊና አማካሪ የነበሩት አቶ ወልደ ሥላሴ ወልደ ሚካኤል ከእስር ተፈቱ፡፡
ከ2006 ጀምሮ በእስር ላይ የነበሩት አቶ ወልደ ሥላሴ በማረሚያ ቤት የነበራቸው ባህሪና ሌሎች መሥፈርቶች ታይተው በአመክሮ መፈታታቸው ተነግሯል፡፡
በሙስና ሰበብ የተከሰሱት የብአዲኑ አቶ መላኩ ፋንታ ግን እስካሁን አለተፈቱም።
በሙስና ክስ ተመስርቶባቸው የነበሩት አቶ ወልደ ሥላሴ ከእስር የተፈቱት ከሁለት ሳምንት በፊት ነው፡፡
ለእስር ያባቃቸው ምክንያት ከዚህ ቀደም ይሠሩበት ከነበረው የደህንነት መሥሪያ ቤት ይከፈላቸው ከነበረው ደመወዝ ጋር በማይጣጣም መልኩ በ175 ካሬ ሜትር ቦታ ላይ ባለ ሦስት ፎቅ ሕንፃ ገንብተው በ50 ሺህ ብር አከራይተው በመገኘታቸው ነው።
አቶ ወልደ ስላሴ ደንቡን ተከትሎ ፈቃድ ሳይሰጣቸው ታጣፊ ክላሽ፣ ኡዚ ጠመንጃና የጭስ ቦምብ በቤታቸው ውስጥ አስቀምጠው መገኘታቸውም ጥፋተኛ እንደነበሩ በክስ ሰነዳቸው ላይ ተመልክቷል
‹‹ሽብርተኝነት በአፍሪካ ቀንድ›› የሚል መጽሐፍ ጽፈው ድርጅቶችና ግለሰቦች በግዳጅ እንዲያሳትሙላቸውና መጽሐፉንም እንዲወስዱ በማድረግ በደህንንነት ስራቸው ጫና አድርገዋል አስፈራርተዋልም ተብሏል።
የመንግሥትን ተሽከርካሪና ነዳጅ በመጠቀም ግለሰቦችን ወደተለያዩ ክልሎች መላክ የሚሉ ክሶችም ቀርበውባቸው እንደነበርም ይታወሳል፡፡
አቶ ወልደስላሴ ከአገዛዙ ጋር በከፍተኛ የደህንነት ሃላፊነት ሲሰሩ ለአቶ መለስ ዜናዊና ለወይዘሮ አዜብ መስፍን የቅርብ ሰው በመሆን ግድያዎችን ጨምሮ በርካታ ወንጀሎችን የፈጸሙ ቢሆንም የተከሰሱት ግን እሳቸውን በሚመለከተው ጉዳይ ብቻ ነው።
ይህም ክሱ ሌሎችን ሰዎች እንዳይነካ ተብሎ መሆኑ ነው የሚነገረው።
አቶ ወልደ ሥላሴ ዓቃቤ ሕግ ያቀረበባቸውን ሊያስተባብሉ ባለመቻላቸው ጥፋተኛ ተብለው በሥር ፍርድ ቤቱ በአሥር ዓመታት እስራት እንዲቀጡም ተወስኖባቸው ነበር፡፡
ከዚህ ወሳኔ በኋላም የሥር ፍርድ ቤቱን ውሳኔ በመቃወም ለፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ብለው የእስር ቅጣቱ ወደ ሰባት ዓመታት ተቀንሶላቸዋል ፡፡
በመሆኑም አቶ ወልደ ሥላሴ ከአራት ዓመታት በላይ በእስር በማሳለፋቸው፣ በማረሚያ ቤት የነበራቸው ባህሪና ሌሎች መሥፈርቶች ታይተው አመክሮ ስለተፈቀደላቸው እስራታቸውን አጠናቀው ከእስር መፈታታቸውን በሀገር ውስጥ የሚታተመውና ለአገዛዙ ቅርበት እንዳለው የሚነገረለት ሪፖርተር ጋዜጣ ዘግቧል ፡፡
ይሕ በእንዲህ እንዳለ በሙስና ሰበብ የተከሰሱት የብአዴኑ አቶ መላኩ ፋንታ ግን እስካሁን አለተፈቱም።ፍርድ ቤቱ ወሳኔ ሳይሰጥ በቀጠሮ በመመላለስ ዓመታትን አስዕጥረዋል።
አቶ ወልደስላሴም ሆኑ ሌሎች የድህንነት ሃላፊዎች ካላቸው ሃብት እና ንብረት አንጻር ሙስና ፈጸሙበት ተብሎ በአቶ ወልደ ስላሴ ላይ የተዘረዘረው ወንጀል ቀልድ ነው ሲሉ ቅርበት ያላቸው ወገኖች በወቅቱ ተችተዋል።ብዙዎቹ የሕወሃት አመራሮች እና የጦር ጄነራሎች ባለህንጻዎች ሲሆኑ በወር በትንሹ ከ300 ሺህ እስከ 500 ሺህ ብር ኪራይ እንደሚሰበስቡም እኒሁ ወገኖች ይገልጻሉ።ጥቂት የማይባሉትም ልጆቻቻወን በምዕራብ ሃገራት ዩኒቨርስቲዎች ከፍለው ያስተምራሉ።