ኢትዮጵያ እና ሱዳን ለኤርትራ መንግስት ተቃዋሚዎች የሚሰጡትን ድጋፍ ሊያጠናክሩ ነው

(ኢሳት ዲሲ–ግንቦት 8/2010) ኢትዮጵያ እና ሱዳን ለኤርትራ መንግስት ተቃዋሚዎች የሚሰጡትን ድጋፍ ለማጠናከር ካርቱም ላይ ስምምነት መፈጸማቸውን ኤርትራ ገለጸች።

ኳታርም ሂደቱን በመደገፍ ተባባሪ መሆኗ ተመልክቷል ።

የኤርትራ ማስታወቂያ ሚኒስቴር ባወጣው ጋዜጣዊ መግለጫ እንዳመለከተው ስምምነቱ የተደረሰው የኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ  በቅርቡ ካርቱምን በጎበኙበት ወቅት  ነው።

የኤርትራ ማስታወቂያ ሚኒስቴር ከትላንት በስቲያ ባወጣው እና በድረገጹ ላይ በለጠፈው መግለጫ  እንዳመለከተው አዲሱ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ሱዳንን በጎበኙበት ወቅት ሁለቱ መንግስታት የኤርትራ መንግስት ተቃዋሚዎችን ለማጠናከር ተስማምተዋል።

የኤርትራ መንግስት ተቃዋሚዎች ግባቸውን እንዲያሳኩ ሙሉ  ድጋፍ ሊድረግላቸው ይገባል በሚል መንግስታቱ መስማማታቸውን የኤርትራ ማስታወቂያ ሚኒስቴር መግለጫ ያስረዳል።

ሁለቱም መንግስታተ አማጽያኑ በድንበራቸው እንዲንቀሳቀሱ ከመፍቀድ ባሻገር የቁሳቁስ ድጋፍ ለማድረግ መስማማታቸውም ተመልክቷል።

ይህንን ለኤርትራ አማጽያን የሚደረገውን ድጋፍ ለማቀናጀት በመንግስታቱ በኩል ተወካዮች መመደባቸውን የዘረዘረው የኤርትራው የማስታወቂያ ሚኒስቴር መግለጫ ኳታርም ሚስተር ቡህራን በተባሉ በኳታር የሚደገፉ ጂሃዲስቶች ዋና አስተባባሪ መወከሏን አመልክቷል።

በኢትዮጵያ በኩል በካርቱም የኢትዮጵያ ኤምባሲ ካውንስለር  ሲመደቡ ፣ሱዳን ደግሞ ጄነራል ሃሚድ አል ሙስጣፋ የተባሉ ሰው መወከሏን የኤርትራ ማስታወቂያ ሚኒስቴር መግለጫ ዘርዝሯል።

ኤርትራ ከትናንት በስቲያ ያወጣቸውን ይህንን መግለጫ በተመለከተ ከሶስቱም መንግስታት እስካሁን  የተሰጠ ምላሸ የለም።

ኤርትራም ክስተቱ አዲስም አስገራሚም እንዳልሆነ ገልጻለች።