ታህሳስ 17 ቀን 2004 ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-በእነ ኤልያስ ክፍሌ የክስ መዝገብ በሽብርተኝነት ወንጀል የተከሰሱት የሀገር ውስጥ ጋዜጠኞች እና የፖለቲካ ፓርቲ የአመራር አባል የማጠቃለያ የክርክር ማቆሚያ በዐቃቤ- ሕግ ጥያቄ በከፍተኛው ፍርድ ቤት ሦስተኛ ወንጀል ችሎት ዛሬ ሳይካሄድ ቀረ፡
የፍትህ ጋዜጣ አምደኛና መምህርት ርዮት ዓለሙ፣ የአውራምባ ታይምስ ጋዜጣ ምክትል ዋና አዘጋጅ ውብሸት ታዬ፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ /አብዴፓ/ ሊቀመንበር አቶ ዘሪሁን ገብረእግዚሃብሄር እና ሂሩት ክፍሌ ለማጠቃለያ ክርክር የቀረቡ ቢሆንም ዐቃቤ- ሕግ “በጽ/ቤት በኩል የተያያዘው የተከሳሾች የመከላከያ የሠነድ ማስረጃ ዛሬ ስለደረሰኝ በአግባቡ ሰነዱን ባልተመለከትኩበት ሁኔታ ማጠቃለያ ክርክር ውስጥ ልገባ አልችልም” ብሏል፡፡
ጋዜጠኛ ርዮት ዓለሙ በበኩሏ “ዐቃቤ- ሕግ ቀደም ሲል የሰነድ ማስረጃዎቹ እንደደረሱት ለፍርድ ቤቱ ገልፆ ነበር፣ አሁን ደግሞ ገና ዛሬ ነው የደረሰኝ የሚልበት አግባብ የለውም” ስትል ተከራክራለች፡፡
ፍርድ ቤቱ የክርክር ማጠቃለያውን ቀደም ብሎ በጽ/ቤት በኩል በጽሑፍ እንዲቀርብለት ያዘዘ ሲሆን፣ ሁኔታውን መርምሮ ብይን ለመስጠት ለጥር 1 ቀን 2004 ዓም ጊዜ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡
የርዮት ጠበቃ አቶ ሞላ ዘገየ “እኛ ብዙ ጊዜ የክርክር ማቆሚያ በቃል ስለሚደረግ ለዚሁ ዝግጁ ነበርን ነገር ግን ፍርድ ቤቱ በጽሑፍ ይሁን ካለን ችግር የለም በጽሑፍ አዘጋጅተን እናቀርባለን” ብለዋል፡፡