(ኢሳት ዲሲ–ግንቦት 6/2010) በአሜሪካን የኢትዮጵያ አምባሳደር ካሳ ተክለብርሃን የጠሩት ስብሰባ በተቃውሞ መበተኑ ተገለጸ።
ባለፈው ቅዳሜ በአሜሪካ ሚኒሶታ ግዛት ብሉሚንግተን ከተማ የተጠራውን ስብሰባ በአካባቢው የሚኖሩ የተለያዩ የኢትዮጵያ ኮሚኒቲዎች ባሰሙት ተቃውሞ ተቋርጧል።
በተለይም የሶማሌ ኢትዮጵያውያን በከፍተኛ ቁጥር ወደ ስብሰባ አዳራሽ በመግባት እንዲቋረጥ ማደረጋቸውን በቪዲዮ ተደግፎ ከወጣው መረጃ ለማወቅ ተችሏል።
አምባሳደር ካሳ ተክለብርሃን ከስብሰባ አዳራሹ በጓሮ በኩል እንዲሸሹ መደረጉንም ያገኘነው መረጃ አመልክቷል።
ያለፈው ቅዳሜ የሚንሶታዋ ቡሉሚንግተን ከተማ ለህወሃት አገዛዝ አባላትና ደጋፊዎች ብቻ ጥሪ የተደረገበት ስብሰባ ልታስተናግድ ቀጠሮ ተይዞላት ነበር።
ዓላማው በቅርቡ አምባሳደር ሆነው የተሾሙት ካሳ ተክለብርሃን የዲያስፖራ ኢትዮጵያውያን ጋር ለመተዋወቅ፣ ስለሀገሪቱ ወቅታዊ ሁኔታ ለመነጋገርና በዚያውም የገንዘብ ማሰባሰብ ፕሮግራም ለማድረግ ነበር።
ወደ አንድ ሺህ የሚጠጋ ታዳሚ በተገኘበት ስብሰባ ላይ የክብር እንግዳው አምባሳደር ካሳ ተክለብርሃን ቦታቸውን ይዘዋል።
ስብሰባው እንደተጀመረ ከአዳራሹ የተቃውሞ ድምጽ መሰማቱን ነው በቦታው የተገኙ ሰዎች የሚገልጹት።
በተለይም የሶማሌ ኮሚኒቲ አባላት እጃቸውን በማጣመር የአብዲ ዒሌ አስተዳደር እየፈጸመ ያለውን ግድያና እስራት እንዲያቆም የሚጠይቁ መልዕክቶች በጽሁፍና በድምጽ መስተጋባት ሲጀምሩ የስብሰባው ሂደት ሊታወክ ችሏል።
ሌሎች ኢትዮጵያውያን የስብሰባው ታዳሚዎችም በኢትዮጵያ እየተፈጸመ ያለው ግፍ ባልቆመበት ስለገንዘብ መዋጮ ስብሰባ አያስፈልግም በሚል በአምባሳደሩ ላይ ግልጽ ተቃውሞ ማቅረባቸውን ነው በቪዲዮ ተደግፎ የደረሰን መረጃ የሚያመለክተው።
ለአዳራሽና ለስብሰባው ማከናወኛ ከፍተኛ ወጪ የወጣበት ይህ ስብሰባ ገቢ መስብሰብ ሳይችል ከመነሻው የተቋረጠ ሲሆን አምባሳደር ካሳ ተክለብርሃንም መድረክ ላይ ወጥተው ሲማጸኑ የሚታይበት ቪዲዮ ተለቋል።
ሆኖም ተቃውሞውን እያቀረበ የነበረው ታዳሚ ስብሰባው መቀጠል የለበትም የሚል አቋም በመያዙ የተነሳ ግጭት ተፈጥሮ የብሉሚንግተን ፖሊስ ወደአዳራሹ መግባቱን ነው ለማወቅ የተቻለው።
ታዳሚው በቁጣ የሃይል ርምጃ መውሰድ መጀመሩን ተከትሎም አምባሳደር ካሳ ተክለብርሃን በጓሮ በር ወጥተው መሄዳቸውም ታውቋል።
የሶማሌ ኮሚኒቲ በሃገር ቤት እየተፈጸመ ያለውን መንግስታዊ ጥቃት በማውገዝ መጠነ ሰፊ ዘመቻ የጀመረ ሲሆን በተለያዩ የዓለም ሃገራት የውግዘት መልዕክቶችን በአብዲ ዒሌ አስተዳደር ላይ በማሰማት ላይ ነው።
በአሜሪካ የኢትዮጵያ አምባሳደር ካሳ ተክለብርሃን ተቃዋሚ ሲገጥማቸው የሚኒሶታው ለመጀመሪያ ጊዜ አይደለም።
በቅርቡም ከ400 በላይ የህወሃት አገዛዝ ደጋፊዎች በሚስጢር በተጋበዙበት የቴሌኮንፍረንስ ውይይት ላይ ኢትዮጵያውያን በመግባት ውይይቱ እንዲስተጓጎል ማድረጋቸው የሚታወስ ነው።
ባለፈው ሳምንትም ተመሳሳይ የቴሌ ኮንፍረንስ ውይይት ተጠርቶ ጥቂት ሰዎች እንደገቡ መስመሩ እንዲዘጋ የተደረገ ሲሆን አብዛኛው ጥሪ የተደረገለት የስርዓቱ ደጋፊ መግባት ሳይችል እንደቀረ ያገኘነው መረጃ ያመልክታል።