(ኢሳት ዲሲ–ግንቦት 3/2010) በሶማሌ ክልል ተቃውሞው በመቀጠል በበርካታ ከተሞች ህዝባዊ ንቅናቄዎች ሲካሄዱ መዋላቸው ተገለጸ።
በጅጅጋ የሚገኘው የክልሉ ጤና ኮሌጅ ተማሪዎችም ተቃውሞ መጀመራቸው ታውቋል።
በቀብሪዳሃር፣ ድሬዳዋ፣ አዲጋላ፣ ቢኬ፣ ኤረርና ሌሎች ከተሞችም በተቃውሞ ውስጥ መዋላቸውን የደረሰን መረጃ አመልክቷል።
በቀብሪዳሃር አንዲት ወጣት በልዩ ሃይሉ መገደሏን ተከትሎም የሕዝብ ቁጣ ተቀስቅሷል።
በሌላ በኩል በአፋር ክልል የህዝባዊ ተቃውሞ ጥሪ ወረቀት መበተኑን የኢሳት ምንጮች ገለጹ።
ህዝቡ ለፍትህና ነጻነት እንዲነሳ የሚጠይቀው ጥሪ በበርካታ የአፋር ክልል የመንግስት መስሪያ ቤቶች መበተኑም ተገልጿል።
በዛሬው የሶማሌ ክልሉ ተቃውሞ በልዩ ሃይል በተወሰደ ርምጃ አንዲት ወጣት ሴት መገደሏ ታውቋል።
በቀብሪዳህር የተነሳውን ተቃውሞ ለማስቆም የሃይል እርምጃ የወሰደው ልዩ ሃይል ጣይሲር ሞሀመድ የተባለችን የ25 ዓመት ወጣት ከቤቷ በመውሰድ የገደላት ሲሆን ራሷን አጠፋች የሚል ምክንያት መሰጠቱ ተቃውሞን አባብሶታል።
በግድያው የተቆጡ የቀብሪዳሃር ከተማ ነዋሪዎች ድንጋይ በመወርወር በልዩ ሃይሉ ላይ ቁጣቸውን ሲያሰሙ እንደነበርም የደረሰን መረጃ አመልክቷል።
በበርካታ የመንግስት መስሪያ ቤቶች ላይም ጥቃት መሰንዘሩን ለማወቅ ተችሏል።
ወጣት ጣይሲር በቀብሪዳሃር የሴቶች ተወካይ በመሆን የምትታወቅ ናት።
በአብዲ ዒሌ አስተዳደር ላይ የተነሳውን ተቃውሞ ከጀርባ ታስተባብራለች በሚል በልዩ ፖሊስ አመራሮች ስትወነጀል እንደነበረ የሚጠቅሱት የኢሳት ምንጮች በመጨረሻም ህይወቷን እንዳጠፉት ገልጸዋል።
አብዲ ዔሌን በመቃወም አቤቱታ ለማሰማት ከሄዱ የሀገር ሽማግሌዎች አንዱ የሆኑት ሰው የጣይሲር አጎት መሆናቸው የገለጹት የኢሳት ምንጮች አብዲ ዒሌ ሽማግሌዎቹን ለማስፈራራት የወሰደው ርምጃም እንደሆነ ገልጸዋል።
ጣይሲር ከተገደለች በኋላ ከተማ መሃል ጥለዋት እንደሄዱም የደረሰን መረጃ አመልክቷል።
የጣይሲር ግድያ በቀብሪዳሃር ተቃውሞውን ወደ አመጽ ሊያሸጋግረው እንደሚችል ነው መረጃዎች የሚያመለክቱት።
በዛሬው ተቃውሞ በርካታ ከተሞች ተሳትፈዋል። በዋና ከተማዋ ጂጂጋ የሚገኘው የጤና ኮሌጅ ተማሪዎች ተቃውሞውን መቀላቀላቸውን ለማወቅ ተችሏል።
ተማሪዎቹ ከቀኑ 10 ሰአት ላይ በጀመሩት ተቃውሞ ፣ የክልሉ ፕሬዝዳን አቶ አብዲ ኢሌ ከስልጣን እንዲወርድ ጠይቀዋል::
ተማሪዎቹ አብዲኢሌን የሚያወግዙ መፈክሮችን ሲያሰሙ፣ የልዩ ሃይል አባላት በፍጥነት በመግባት ተማሪዎች ተቃውሞውን እንዲያቆሙ ጠይቀዋል::
ዙሪያዋን በሰሞንኛው ተቃውሞ ተከባ የሰነበተችው ጂጂጋ በሶማሌ ክልል ወጣቶች በርባራታዎች የሚደረገውን ህዝባዊ ንቅናቄ መቀላቀሏ ለአብዲ ዒሌ አስተዳደር ትልቅ ፈተና እንደሚሆን ተገልጿል።
በድሬዳዋ ዙሪያ በሽንሌ ዞን የተለያዩ መንደሮች፡ ተቃውሞ ሲካሄድ ነው የዋለው።
የሶማሌ ክልሉ ህዝባዊ ንቅናቄ ዕምብርት በሆነችው ሽንሌ ዞን ዛሬም ተቃውሞ የተደረገ ሲሆን በርካታ ሰዎች መታሰራቸው ተገልጿል።
ልዩ ፖሊስ የሽንሌ ከተማን መወረሩም ታውቋል።
ቤት ለቤት ፍተሻ በማድረግ በተለይ ሴቶች ላይ ከፍተኛ ድብደባ መፈጸሙን የደረሰን መረጃ አመልክቷል።
ገረት ኩልምዬ የተባሉ የጎሳ መሪ በአብዲ ዒሌ ትዕዛዝ ታፍነው ከተወሰዱ በኋላ ከፍተኛ ድብደባ ተፈጽሞባቸዋል።
መሀመድ አዴ የተባሉ ታዋቂ ነጋዴም ከታፈኑ በኋላ ወደአልታወቀ ቦታ መወሰዳቸው ታውቋል።
የሶማሌ ክልሉ ተቃውሞ በ11ዱም የክልሉ ዞኖች የተዳረሰ ሲሆን አብዲ ዒሌ በአስቸኳይ ከስልጣን እንዲወርድ በመጠየቅ ተጠናክሮ ቀጥሏል።
በሌላ በኩል በአፋር ህዝባዊ ንቅናቄ ለማቀጣጠል ጥሪ የሚያደርግ ወረቀት መበተኑን ለኢሳት የደረሰ መረጃ አመለክቷል።
በአሳይታና ሰመራ በመንግስት መስሪያ ቤቶች ሳይቀር የተበተነው ወረቀት የአፋር ህዝብ ጭቆና በቃኝ ብሎ እንዲነሳ የሚጠይቅ ነው።
ወረቀቱን የበተነው አካል ማን እንደሆነ ግን አልታወቀም።