አንዷለም አራጌ በጀርመን የጀግና አቀባበል ተደረገለት

(ኢሳት ዲሲ–ግንቦት 3/2010)የፖለቲካና የነጻነት ታጋዩ አንዷለም አራጌ ዛሬ በጀርመን ፍራንክፈረት የጀግና አቀባበል ተደረገለት።

አንዷለም አራጌ ለሕዝብ መብት ባደረገው ትግል በኢትዮጵያው አገዛዝ የእድሜ ልክ ፍርደኛ ነበር።

የነጻነት ታጋዩ አንዷለም አራጌ ከ6 አመታት በላይ በእስር ሲማቅቅ ከቆየ በኋላ በቅርቡ በሕዝብ ተቃውሞ ከሌሎች የሕሊና ታጋዮች ጋር መለቀቁ ይታወሳል።

በሽብር ክስ ተመስርቶበት እድሜ ልክ ተፈርዶበት ነበር።

ከፍርዱ በኋላም 6 አመታትን በወህኒ ሲማቅቅ ቆይቶ በሕዝብ ትግል ከእስር ተፈቷል።

ከእስር የተፈታው ፖለቲከኛ አንዷለም አራጌ ዛሬ ወደ ጀርመን ፍራንክፈርት አቅንቷል።

በአውሮፕላን ማረፊያውም ሲደርስ የጠበቀው የጀግና አቀባበል ነበር።

በጀርመን ፍራንክፈርትና አካባቢው የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን የኢትዮጵያን ሰንደቅ አላማ በመያዝና የተለያዩ ሃገራዊ አልባሳትን በመልበስ በደማቅ አቀባበል ተቀብለውታል።

አጼ ቴድሮስ የተሰውበትን 150ኛ አመት በማስመልከት በተዘጋጀው ስነስርአት ላይ በክብር እንግድነት የተጋበዘው አንዱአለም አራጌ በተደረገለት ደማቅ አቀባበል መደሰቱን ገልጿል።

የትግላችንን ውጤት በጥቂቱም ቢሆን ማየት የቻልን ቢሆንም ነገር ግን አንዳችም የተጨበጠ ነገር ባለመኖሩ ትግሉን አጠናክሮ መቀጠል እንደሚገባ መልዕክቱን አስተላልፏል።

ግብዣውን ያደረገለትና የፕሮግራሙ አዘጋጅ በጀርመን የኢትዮጵያውያን ትብብር መድረክ መሆኑ ታውቋል።

ነገ ሌሎች ተጋባዥ እንግዶች በሚገኙበት ጥናታዊ ጽሁፎች እንደሚቀርቡና አቶ አንዱአለም አራጌም ንግግር እንደሚያደርጉ ከመርሃ ግብሩ ለማወቅ ተችሏል።