የ62 ተከሳሾች ክስ ተቋረጠ

(ኢሳት ዲሲ–ግንቦት 3/2010)በቂሊንጦ ቃጠሎ ከተከሰሱ 38 ሰዎች መካካል በሰው መግደል ወንጀል ተጠረጥረዋል ከተባሉት በስተቀር 26ቱ ክሳቸው እንዲነሳ ተወሰነ።

ዶክተር ፍቅሩ ማሩንና የመቶ አለቃ ማስረሻ ሰጤን ጨምሮ በጠቅላላው የ62 ተከሳሾች ክስ እንዲነሳ ተወስኗል።

በተለያዩ ጉዳዮች ተወንጅለው ከተከሰሱ ታዋቂ ሰዎች መካከል እስካሁን አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ አልተፈቱም።

የኢትዮጵያ አየር ሃይል አብራሪ የመቶ አለቃ በሃይሉ ገብሬም ዕድሜ ልክ ተፈርዶበት ወህኒ ቤት ይገኛል።

የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ እንዳስታወቀው ዶክተር ፍቅሩ ማሩን ጨምሮ ክሳቸው የተነሳላቸው 62 ተከሳሾች ጉዳያቸው በፍርድ ሂደት ላይ ያለና እንዲከላከሉ የተወሰነባቸው ናቸው።

የአቃቤ ህግ መረጃ እንደሚያመለክተው በእነ ማስረሻ ሰጤ መዝገብ በቂሊንጦ  ቃጠሎ ከተከሰሱት 38 ሰዎች መካካል አራቱ በሰው መግደል ወንጀል ክስ ቀርቦባቸው እንዲከላከሉ ተወስኖባቸዋል።

ቀሪዎቹ 8ቱ በነጻ እንዲሰናበቱም መወሰኑ ይታወሳል። 26ቱ ደግሞ የወንጀል ሕግን በመተላላፍ እንዲከላከሉ የተወሰነባቸው ናቸው።

እናም ከ30 ተከሳሾች 26ቱ ክሳቸው እንዲነሳ ሲደረግ በሰው መግደል ወንጀል ተጠርጥረዋል የተባሉ አራቱ ግን የፍርድ ሂደታቸው እንዲቀጥል ተውስኗል።

ክሳቸው እንዲቋረጥ የተወሰነላቸው መቶ አለቃ ማሰረሻ ሰጤን ጨምሮ አራቱ ሰዎች  ዛሬ ወደ ማሰቃያ ቦታ ወደ ዝዋይ መወሰዳቸውም ተነግሯል።

በተያያዘ ዜና በእነ ቴድሮስ ዳንኤል መዝገብ የወንጀለኛ ሕጉን በመተላላፍ ጉዳያቸው በፍርድ ሂደት ላይ ያለ 18 ሰዎች ክሳቸው እንዲነሳ ተብሏል።

በዚሁም መሰረት በጠቅላላው 62 ሰዎች ክሳቸው እንዲነሳ በመባሉ ዶክተር ፍቅሩ ማሩን ጨምሮ ተጠርጣዎቹ በነጻ እንደሚለቀቁ ይጠበቃል።

በኢትዮጵያ የተካሄደውን ሕዝባዊ ተቃውሞ ተከትሎ በርካታ ታዋቂ ፖለቲከኞችና ጋዜጠኞች እንዲሁም ምሁራን ሲለቀቁ  አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ አልተፈቱም።

የኢትዮጵያ አየር ሃይል አብራሪ የመቶ አለቃ በሃይሉ ገብሬም ዕድሜ ልክ ተፈርዶበት ወህኒ ቤት ይገኛል።

ሌሎች ለጊዜው ስማቸው ያልተገለጸ በርካታ የፖለቲካ እስረኞች አሁንም በተለያዩ እስር ቤቶች በመሰቃየት ላይ መሆናቸው ይታወቃል።