(ኢሳት ዲሲ–ሚያዚያ 22/2010) በደቡብ አፍሪካ ከሃገሪቱ ዜጋ ውጪ ባልተለመደና በደመቀ መልኩ የተከናወነው የገዛህኝ ነብሮ የቀብር ስነስርአት በዙዎችን ያስደነቀ ሆኖ ማለፉ ተገለጸ።
የደቡብ አፍሪካ ብሔራዊ ቴሌቪዥንም ለቀብር ስነስርዓቱ የዜና ሽፋን በመስጠት ኢትዮጵያውያን የማህበረሰብ መሪያቸውን በታላቅ ሀዘን ሸኙት ሲል በዘገባው አስደምጧል።
የአክቲቪስት ገዛህኝ ገብረመስቀል ነብሮ የቀብር ስነስርዓት በደቡብ አፍሪካ ብቻ ሳይሆን በብዙዎች ዘንድ መነጋገሪያ መሆኑ ተሰምቷል።
የቀብር ስነስርዓቱንም የደቡብ አፍሪካ ፖሊስ በልዩ ሁኔታ አጅቦታል።
በመላው ዓለም በ50 ከተሞች በተከበረው የኢሳት 8ኛው ዓመት በዓል ላይም አክቲቪስት ገዛህኝን በተመለከተ የመታሰቢያ ፕሮግራም መካሄዱ ታውቋል።
ቅዳሜ ሚያዚያ 13 በአንድ የደቡብ አፍሪካ ነፍሰ ገዳይ በተተኮሰበት ጥይት ህይወቱ አለፈ።
በሳምንቱ ቅዳሜ በደመቀ ስነስርዓት የቀብር ስነስርዓቱ ተፈጸመ- አክቲቪስት ገዛሀኝ ገብረመስቀል ነብሮ።
በመላው ዓለም በሚገኙ ኢትዮጵያውያን ዘንድ የአክቲቪስት ገዛህኝ ግድያ ከሀዘን ባለፈ ቁጭትን የሚፈጥር ሆኗል።
በደቡብ አፍሪካ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ግድያው በህወሃት አገዛዝ በተቀነባበረ መልኩ የተፈጸመ እንደሆነ ይገልጻሉ።
ፖሊስ ግድያውን በማጣራት ላይ ሲሆን እስካሁን ከግድያ ጀርባ ያለው ማን እንደሆነ በምርመራ አልተረጋገጠም።
በፕሪቶሪያ የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ሀዘኑን ገልጾ ግድያውን በተመለከተ የሚሰጠው አስተያየት ወንጀለኛውን ለመደበቅ የሚደረግ ሙከራ ነው ሲል የሚቀርብበትን ክስ አስተባብሏል።
የአክቲቪስት ገዛህኝ ግድያና በደቡብ አፍሪካ ኢትዮጵያውያን ሀዘናቸውን የገለጹበት ትዕይንት መነጋገሪያ ሆኖ ነው ሳምንቱን የዘለቀው።
ባለፈው ዓርብ በልዩ ስነስርዓት የመታሰቢያ ፕሮግራም የተካሄደ ሲሆን ከተለያዩ የዓለም ሀገራት የተወከሉ ኢትዮጵያውያን መልዕክት በማስተላለፍ ለአክቲቪስት ገዛሀኝ ያላቸውን አክብሮትና ፍቅር አሳይተዋል።
በማግስቱ ቅዳሜ ሚያዚያ 20 የተከናወነው የቀብር ስነስርዓት ኢትዮጵያውያን ለገዛሀኝ ያላቸውን ልዩ ስሜት ያሳዩበት አጋጣሚ ከመሆን ባለፈ ለሀገራቸው ፍትህና ነጻነት የሚከፍሉት ዋጋ እስከምን እንደሚደርስ ለወዳጅና ጠላት ያረጋገጡበት መሆኑም ተገልጿል።
የአክቲቪስት ገዛሀኝ ነብሮ የቀብር ስነስርዓት በደቡብ አፍሪካ ለሀገሬው ታዋቂ ፖለቲከኞችና ዝነኛ ሰዎች ከሚደረገው ስነስርዓት ጋር ተመሳሳይ በመሆኑ በልዩ ትኩረት እየተነሳ ነው።
በኢትዮጵያ ሰንደቅዓላማ ያሸበረቀውና በብዙ ሺህ የሚቆጠር ህዝብ የታደመበት የአክቲቪስት ገዛህኝ ነብሮ የቀብር ስነስርዓት በደቡብ አፍሪካ ብሔራዊው ቴሌቪዥን ሽፋን የተሰጠው ሲሆን ኢትዮጵያውያን ታላቅ የማህበረሰብ መሪያቸውን በደመቀ ሽኝት ተሰናበቱት ሲል ዘገባውን አቅርቧል።
በደቡብ አፍሪካው ብሔራዊ ቴሌቪዥን በቀረበው ዜና ላይ የአክቲቪስት ገዛህኝ ሴት ልጅ ሜላት ገዛህኝ ስለአባቷ ጀግንነት በመናገር የሱን ህልም ከዳር ለማድረስ የምችለውን አደርጋለሁ ማለቷ ተጠቅሷል።
በደቡብ አፍሪካ ጆሀንስበርግ በሳምንቱ የእረፍት ቀናት መነጋገሪያ ሆኖ የሰነበተው የአክቲቪስት ገዛህኝ የቀብር ስነስርዓት ዋናውን የከተማዋን መንገድ ለሰዓታት እንዲዘጋ ያደረገ መሆኑም ተገልጿል።
የደቡብ አፍሪካ ፖሊስም በተለየ ትኩረት ለስነስርዓቱ ጥበቃ ማደረጉን ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
በማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ አንዳንድ የደቡብ አፍሪካ ተወላጆች የቀብር ስነስርዓቱን ትዕይንት በተመለከተ አድናቆታቸውን በመግለጽ ይህ ሁሉ የተደተረገለት ሰው ማን ነው ሲሉ መጠየቃቸውን ነው ለማወቅ የተቻለው።
በሌላ በኩል በዓይነቱ ልዩ በሆነውና በ50 ከተሞች በአንድ ቀን በተከበረው የኢሳት ስምንተኛ ዓመት ክብረ በዓል ላይም ለአክቲቪስት ገዛህኝ ደማቅ የመታሰቢያ ፕሮግራም መደረጉን ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
አክቲቪስት ገዛህኝ ህይወቱ ከማለፉ ከደቂቃዎች በፊት በደቡብ አፍሪካ ለሚዘጋጀው የኢሳት ክብረበዓል ቲኬቶችን ለማከፋፈል ተዘጋጅቶ እንደነበረ መገለጹ የሚታወስ ነው።