በአፍጋኒስታን በተፈጸመ ጥቃት 29 ሰዎች ተገደሉ

(ኢሳት ዲሲ–ሚያዚያ 22/2010) በአፍጋኒስታን ርዕሰ መዲና ካቡል አሸባሪዎች ባደረሱት ጥቃት ጋዜጠኞችን ጨምሮ 29 ሰዎች ተገደሉ።

የአፍጋኒስታን የጤና ጥበቃ ባለስልጣናት እንደገለጹት ከሁለት ተከታታይ ፍንዳታዎች በኋላ ከሞቱት 29 ሰዎች በተጨማሪ 49 ሰዎች ቆስለዋል።

አለም አቀፉ የአሸባሪ ቡድን አይሲስ በጥቃቱ ሃላፊነትን ወስዷል።

ዛሬ ሰኞ ማለዳ በአፍጋኒስታን ርዕሰ መዲና ካቡል በደረሰው የሽብር ጥቃት የመጀመሪያው ፍንዳታ አንድ ሞተር ቢስክሌት በሚያሽከረክር ግለሰብ በሃገሪቱ የጸጥታ መስሪያ ቤት አካባቢ በፈጸመው የአጥፍቶ መጥፋት ርምጃ መሆኑ ታውቋል።

2ኛው ጥቃትም በተመሳሳይ ቦታ ከ30 ደቂቃ በኋላ መፈጸሙ ተመልክቷል።

በአጠቃላይ በዚህ አደጋ ጋዜጠኞችንና የሕክምና ሰራተኞችን ጨምሮ 29 ሰዎች ሲገደሉ 49 ደግሞ መቁሰላቸውን አልጀዚራ ዘግቧል።

እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር መስከረም 11/2001 በአሜሪካ የደረሰውን የሽብር ጥቃት ተከትሎ አፍጋኒስታን ላይ በተወሰደው የሃይል አጸፋ ሃገሪቱ ላለፉት 17 አመታት በቀውስ ውስጥ ትገኛለች።

የአሜሪካውያን የሽብር ጥቃት በመፈጸም ዋና ተዋናይ የሆነውን የአልቃይዳውን መሪ ቢላደንን ደብቃለች በሚል በአፍጋኒስታን ላይ በተወሰደባት የሃይል ርምጃ በሙላ መሃመድ ኦማር የሚመራው የአፍጋኒስታን የታሊባን አገዛዝ መፍረሱ ይታወቃል።