(ኢሳት ዲሲ–ሚያዚያ 16/2010) በሶማሌ ክልል ሽንሌ ዞን የተነሳው ህዝባዊ ተቃውሞ ወደ ሌሎች ዞኖችም በመዛመት ላይ መሆኑ ታወቀ።
የክልሉ ፕሬዝዳንት አብዲ ዒሌ ከስልጣን እንዲወርዱና ፍትህና ነጻነት እንዲሰፍን በሽንሌ አራት ወረዳዎች የተጀመረው ተቃውሞ ዛሬ ደገሀቡር መግባቱን ለኢሳት የደረሰው መረጃ አመልክቷል።
የክልሉ ልዩ ሃይል ተቃውሞውን ለማስቆም የሃይል ርምጃ ተጠቅሞ ከ100 በላይ ሰዎች መታሰራቸው ተገልጿል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ የሶማሌ ክልል ፕሬዝዳንት ዛሬ ሹሙትና የካቢኔ ሽግሽግ አድርገዋል።
ከህዝባዊ ወያኔ ሃርነት ትግራይ ህወሃት ጄነራሎች ጋር ወዳጅነታቸው የጠበቀ ነው።
በዚህም የህወሃትን ጥቅም ለማስጠበቅ በሶማሌ ክልል ህዝብ ላይም ሆነ በሌላው የኢትዮጵያ ህዝብ ላይ መጠነ ሰፊ የሰብዓዊ መብት ጥሰት በመፈጸም ስማቸው ይነሳል።
የክልሉ ፕሬዝዳንት ሆነው በቆዩባቸው ባለፉት 10 ዓመታት በስጋና በጋብቻ የሚዛመዷቸውን ሰብስበው ከላይ እስከታች ስልጣን በማከፋፈል ካቢኔአቸውን የቤተሰብ ጉባዔ አድርገውታል ተብለው ይከሰሳሉ።
የሚቀናቀኗቸውን የሚያስሩበትና የሚያሰቃዩበት ጄል ኦጋዴን የተሰኘ እስር ቤት አላቸው። የሶማሌ ክልሉ ፕሬዝዳንት አብዲ መሃመድ ኡመር ዒሌ።
የሶማሌ ክልል ህዝብ በእሳቸው የስልጣን ዘመን ከፍተኛ ስቃይና መከራ እንደገጠመው ይናገራል።
ከግማሽ ሚሊየን በላይ የክልሉ ነዋሪ በረሃብ አለንጋ እየተገረፈ በካምፕ እንዲኖር ተፈርዶበታል።
በመቶ ሺዎች የሚቆጠር ህዝብ ለስደት ተዳርጓል።
ድህነት፣ የሰላም እጦት፣ ስራ አጥነት፣ የኑሮ ውድነት፣ በአጠቃላይ በዘርፈ ብዙ ችግሮች የተተበተበው የሶማሌ ክልል ህዝብ የአብዲ ዒሌን አገዛዝ ለመገላገል ካለፈው ሳምንት አንስቶ ተቃውሞ አንስቷል።
በተለይም የሽንሌ ዞን አራት ወረዳዎች የአብዲ ዒሌን አስተዳደር በመቃወም የተጀመረው ህዝባዊ ንቅናቄ የየወረዳዎቹን መንግስታዊ መዋቅሮች በማፍረስ ባለስልጣናት አካባቢውን ለቀው እንዲሄዱ አድርጎአቸዋል።
እስር ቤት ተሰብሮም በርካታ እስረኞች ተለቀዋል።
በሽንሌ ዞን የተጀመረው የህዝብ ንቅናቄ በተያዘው ሳምንት ወደሌሎች አካባቢዎችም መዛመቱን ነው በፌደራል ፖሊስ የቀድሞ የድሬዳዋ ፖሊስ ሻለቃ ዐሊ ሰሚሬ ሲጋድ ለኢሳት የገለጹት።
ተቃውሞ እስከ ጂጂጋ ሊደርስ እንደሚችልና አብዛኞቹን አካባቢዎች በማዳረስ በከፍተኛ እልህና ቁጣ እየተዛመተ መሆኑንም ገልጸዋል።
በሽንሌ ዞን ለተከታታይ ቀናት ሲካሄድ የቆየውን ተቃውሞ ተከትሎ ወታደራዊ እዙ በቀጥታ የሚያዛቸው ወታደሮች አካባቢውን እንዲቆጣጠሩት መደረጉ ታውቋል።
በክልሉ መሪ አቶ አብዲ ኢሌ በቀጥታ የሚታዘዙት የልዩ ሃይል አባላት አካባቢውን ተቆጣጥረው የቆዩ ሲሆን፣ እነዚህን ሚሊሺያዎች በመተካት የክልሉ ኮማንድ ፖስት ከትላንት ጀምሮ አካባቢውን እንደሚቆጣጠረው ለህዝቡ ተናግረዋል።
ለተከታታይ ቀናት በተደረገው ተቃውሞ ወጣቶች እስር ቤቶችን ሰብረው በመግባት እስረኞችን አስፈትተዋል።
በአካባቢው የተጀመረውን ተቃውሞ ተከትሎ ባለስልጣናት በመሸሻቸው አብዲ ኢሌና ሌሎች ወታደራዊ አዛዦች ህዝቡ ተቃውሞውን እንዲያቆም ሲማጸኑ ሰንብተዋል።
ሆኖም ተቃውሞው ቀጥሎ የክልሉን ዋና ከተማ ጅጅጋን እየተጠጋት መሆኑን የደረሰን መረጃ አመልክቷል።
አብዲ ዒሌ ጉዳዩን ከሽብርተኝነት ጋር በማያያዝ በህዝቡ የተፈጸመ በማስመሰል አደጋ ለመጣል እያሴሩ በመሆናቸው ጥንቃቄ እንዲደረግ መልዕክት ተላልፏል።
በተለይም የባቡር መስመር ላይ ጥቃት በመሰንዘር የህዝቡን ተቃውሞ አቅጣጫ ለማሳት የታቀደ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል።
በሌላ በኩል ህዝባዊ ተቃውሞ የሚንጣቸው የሶማሌ ክልል ፕሬዝዳን አብዲ ዒሌ ካቢኒያቸውን አፍርሰዋል።
21 የካቢኔ አባላትን በማባረር በምትካቸው ሌሎችን መሾማቸውን የደረሰን መረጃ አመልክቷል።
ከ 5 ሃላፊዎች በቀር ከምክትል ፕሬዝዳንት ጀምሮ ያሉት የካቢኔ አባላት በሙሉ ከስልጣናቸው የተወገዱ ሲሆን በፓርቲያቸውም ውስጥ ቁልፍ ቦታ የያዙ ሰዎችን አባረዋል።
በክልሉ እየተካሄደ ካለው የህዝብ ተቃውሞ ጋር እንደሚያያዝ የገለጹት የኢሳት ምንጮች የህወሃት ጄነራሎች የሚመሩት ሰራዊት ከጎናቸው በመሆን ድጋፍ እየሰጣቸው እንደሆነም ጠቅሰዋል።