በኢትዮጵያ 8 ሚሊየን ሕዝብ አስቸኳይ እርዳታ ካላገኘ ሕይወቱ አደጋ ላይ ነው ተባለ

(ኢሳት ዲሲ–ሚያዚያ 16/2010) በኢትዮጵያ የምግብ እርዳታ የሚፈልጉ 8 ሚሊዮን ኢትዮጵያውያን አስቸኳይ እርዳታ ካላገኙ ሕይወታቸው አደጋ ላይ መሆኑ ተነገረ።

የአለም የምግብ ፕሮግራም ይፋ ባደረገው የአስቸኳይ ጊዜ ሪፖርት እንደተመለከተው 1 ነጥብ 8 ሚሊየን የሶማሌ ክልል ነዋሪ ኢትዮጵያውያን በሕይወት ለመቆየት አስቸኳይ የምግብ እርዳታ ያስፈልጋቸዋል።

የአለም የምግብ ፕሮግራም ይፋ ባደረገው የአደጋ ጊዜ ሪፖርት በዚህ በተያዘው የምዕራባውያኑ 2018 ዓመተ ምህረት 7 ነጥብ 9 ሚሊየን ኢትዮጵያውያን አስቸኳይ የምግብ እርዳታ ያስፈልጋቸዋል።

ምግብ ነክ ያልሆኑ እርዳታዎችን ሲጨምር ደግሞ የተረጂዎች ቁጥር 16 ሚሊየን ይደርሳል።

ይህንን የእርዳታ ፈላጊዎች ፍላጎት ለማሟላት እስከመጪው መስከረም ወር የሚያስፈልገው ገንዘብ 218 ሚሊየን የአሜሪካን ዶላር መሆኑም ታውቋል።

እስካሁን የተገኘውም 125 ሚሊየን ዶላር መሆኑን የአለም የምግብ ፕሮግራም አስታውቋል።

ከዚህ 125 ሚሊየን ዶላር እርዳታ 57 ነጥብ 34 ሚሊየን ዶላር ከአሜሪካ የተገኘ ሲሆን ካናዳ፣ስዊዲን፣ጀርመንና ጃፓን ከ10 እስከ 3 ሚሊየን ዶላር መለገሳቸውም ተመልክቷል።

በዚህ በተገኘው ድጋፍ በሶማሌ ክልል ለ3 ነጥብ 7 ሚሊየን ኢትዮጵያውያን የምግብ እርዳታ ተለግሷል።

በተለይ ለ1 ሚሊየን ሕጻናትና እናቶቻቸው እንዲሁም ለነፍሰጡር እናቶች የተመጣጠነ ልዩ ምግብ መቅረቡን የአለም የምግብ ፕሮግራም አስታውቋል።

በይበልጥ በሶማሌ ክልል ላይ የበረታውንና ወደ 8 ሚሊየን ኢትዮጵያውያንን ለአደጋ ያጋለጠውን ችግር ለመቅረፍ የአለም ምግብ ፕሮግራም የእርዳታ ጥሪውን ቀጥሏል።

ተረጂዎቹ የተባለውን እርዳታ ካላገኙ ህይወታቸው አደጋ ላይ እንደሚሆን የአለም ምግብ ፕሮግራም አስጠንቅቋል።