በአማራ ክልል ባሉ ከተሞች የነዳጅ እጥረት ተከሰተ

(ኢሳት ዲሲ–ሚያዚያ 16/2010) በአማራ ክልል ባሉ ከተሞች ከፍተኛ የነዳጅ እጥረት መከሰቱ ተነገረ።

በዚህም ሳቢያ በየአካባቢዎቹ የትራንስፖርት መስተጓጎል ተፈጥሯል።

የነዳጅ እጥረቱ መንስኤ ምን እንደሆነ በውል ባይታወቅም ችግሩ ከውጭ ምንዛሬ እጥረት ጋር የተያያዘ ሊሆን እንደሚችል የአካባቢው ምንጮች ይናገራሉ።

በባህርዳር ፣ ወረታ ፣ጎንደር ፣ ደብረታቦር ፣ ወልዲያ ፣ ደብረማርቆስ ፣ ኮሶበርና መሰል ከተሞች ቤንዚንና ናፍጣ በነዳጅ ማደያዎች ባለመኖሩ የትራንስፖርት ችግር ተፈጥሯል።

የኢሳት ምንጮች እንዳሉት ቤንዚን አለ በተባለበት ማደያ ከጠዋት ጀምሮ ረጃጅም ሰልፎች ተከስተዋል።

በተለይ ደግሞ ባጃጆች እና የከተማ ታክሲዎች በብዛት ተሰልፈው ይታያሉ ነው የተባለው።

የአካባቢው ምንጮች እንደገለጹት የተወሰኑ  ባለ ባጃጆች  በባህርዳር ዙሪያ ባሉ ከተሞች የተወሰኑ ሊትሮችን አስመጥተው የትራንስፖርት ታሪፍ በመጨመር እየሰሩ ይገኛሉ።

ዛሬ ነዳጅ አለ ተብሎ ረጅም የተሽከርካሪ ሰልፍ ከሚታይበት የባህርዳር የነዳጅ ማደያዎች መካከል ፓፒረስ ሆቴል ስር ያለው አንዱ ነው።

በባህርዳር ትናንት በፖፒረስ ሆቴል ስር ባለው የነዳጅ ማደያ  በነበረው ሰልፍ በጀሪካን ለመቅዳት የጠየቁ ወጣቶች በስፍራው በነበረው የልዩ ሃይል ፖሊስ ክፉኛ መደብደባቸው ተሰምቷል።

ከዚህም በኋላ ነዳጅ ማለቁ እና ብዛት ያላቸው ባጃጆችን እየገፉ ወደ ማሳደሪያ ስፍራ እንደወሰዷቸው ታውቋል።

ሌሎች በቀበሌ 14 የተባበሩት ፣ በቀበሌ 10 አጂፕ ፣በቀበሌ 9 ቶታል ጨምሮ ከ10 በላይ ማደያዎች ነዳጅ ባለመኖሩ ከአገልግሎት ውጪ ናቸው።

መረጃዎች እንደሚያመለክቱት የነዳጅ መጥፉት የመላ አማራ ከተሞችን እያዳረሰ ነው !!

እናም ቤንዚንና ናፍጣ ባለመኖሩ የትራንስፖርት እንቅስቃሴ እየተገታ ነው  ተብሏል ።

የነዳጅ እጥረቱ መንሳኤ ምን እንደሆነ በውል ባይታወቅም ችግሩ ከውጭ ምንዛሬ እጥረት ጋር የተያያዘ ሊሆን እንደሚችል የአካባቢው ምንጮች ይናገራሉ።